የኢትዮጵያ ብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ትግራይን መልሶ ለማቋቋም የ10 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ

146

የካቲት 20 /2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት የትግራይ ክልልን መልሶ ለማቋቋም የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ የ10 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ።

ድጋፉን የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጄነራል ተመስገን ጥሩነህ ዛሬ አስረክበዋል።

አቶ ተመስገን ድጋፉን ባስረከቡበት ወቅት እንደተናገሩት፤ የተደረገው ድጋፍ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ሁሉም አካላት የትግራይ ክልልን መልሶ ለማቋቋም ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ ማድረጋቸውን ተከትሎ ነው።

ዳይሬክተር ጄነራሉ የተደረገው ድጋፍ በትግራይ በነበረው ህግን የማስከበር ዘመቻ በክልሉ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች እንደሚውል ተናግረዋል።

ድጋፉ የመጀመሪያ መሆኑን የገለጹት አቶ ተመስገን፤ "ወደ ፊት እንደ አስፈላጊነቱ ድጋፉ የሚቀጥል ይሆናል" ብለዋል።

ከሰብአዊ ድጋፉ በተጨማሪ በክልሉ የጸጥታ ሥራውንና ግንኙነትን ለማጠናከር ከዚህ በፊት ተገዝተው በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ክልሉ ያልተላኩ የመገናኛ ራዲዮኖችን ለመላክ ዝግጀት እየተደረገ መሆኑንም አቶ ተመስገን አያይዘው ገልጸዋል።

ድጋፉን የተረከቡት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትርና የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር ዶክተር አብርሃም በላይ ትግራይን መልሶ ለማቋቋም ለተደረገው የገንዘብ ድጋፍ አመስግነዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት በህግ ማስከበር ዘመቻ ወቅትና ከህግ ማስከበር በኋላ በክልሉ በርካታ መልካም ተግባራት እየሰራ መሁኑንም ተናግረዋል።

"በዚህም ተቋሙ የህዝብ መሆኑን በተግባር እያስመሰከረ ይገኛል" ብለዋል ዶክተር አብርሃም።በአሁኑ ወቅት የትግራይ ክልል ህዝብ የሁሉንም ድጋፍ እንደሚፈልግ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም