"የአድዋ ድል በአንድነት መንፈስ እንደተገኘ ሁሉ ለአገር በአንድነት መቆም ይገባል" - ፕሬዚደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ

60

የካቲት 20/2013 (ኢዜአ) የአድዋ ድል ያለ ዘር፣ ሐይማኖትና የአካባቢ ልዩነት እንደተገኘ ሁሉ በዚህ ዘመንም ከአድዋ በመማር ለአገር አንድነት መቆም እንደሚገባ ፕሬዚደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ አሳሰቡ።

የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ አምባሳደሮች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ አባ ገዳዎች፣ የኃማኖት አባቶች፣ ከአገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች የመጡ ወጣቶችና ሌሎች አካላት የተሳተፉበት ብሔራዊ የልሂቃን ምክክር በወዳጅነት ፓርክ እየተካሄደ ነው።

በመርሃ ግብሩ ንግግር ያደረጉት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ፤ የምክክር መድረኩ 125ኛው የአድዋ ድል በዓል በኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን ባሉበት የዓለም ክፍል ሁሉ እየተከበረ ባለበት ወቅት መካሄዱ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።

የአድዋ ድል ለጋራ ዓላማ የአንድ አገር ሕዝብ ልዩነቶቹን በመተው እንዴት በአንድነት መቆም እንደሚቻል ያሳየበት ብቻ ሳይሆን አገርን ከወራሪ ለመከላከል ውድ ሕይወትን መሰዋትን ያስተማረበት ነው ብለዋል።

የአድዋ ድል ያለዘር፣ ሐይማኖትና የአካባቢ ልዩነት እንደ ተገኘ ሁሉ በዚህ ዘመንም ከአድዋ በመማር ያለ ልዩነት መቆም እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

"ለማንኛውም ስራችን የአድዋን መንፈስ መላበስ አለብን፤ ኢትዮጵያዊያን በአገር ግንባታ ላይ ምን ሚና አለኝ ብለን ልንሰራ ይገባል" ብለዋል ፕሬዚዳንቷ።

የአድዋ ድል በተለየ ሁኔታ በአገር አቀፍ ደረጃ በሁሉም ቦታዎች በደማቅ ሁኔታ እተከበረ መሆኑን አውስተዋል።

ድሉ በአገር አቀፍ ደረጃ መዘከሩም ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል።

ኢትዮጵያዊያን በወቅቱ በአንድነት በመቆም የፈጸሙትን አኩሪ ገድል የአሁኑ ትውልድም መላበስ እንደሚገባውም አሳስበዋል።

በአብሮነት ለመኖርና ለማደግ ብሔራዊ ምክክር በማድረግ ብሔራዊ መግባባት ላይ ከመድረስ ውጭ ሌላ አማራጭ እንደሌለም አጽንኦት ሰጥተዋል።

"ብሔራዊ ምክክር ማድረግ ድርድር አይደለም፣ እርቅ መፈለግ አይደለም፣ የመወያየትና የመግባባት መድረክ ነው" ያሉት ፕሬዚዳንቷ መፍትሔ የሚገኘውም በመወያየትና በመግባባት ለአገር ጽኑ መሰረት መጣል ሲቻል እንደሆነ አመላክተዋል።

በጋራ በመገናኘት ሌላውን ለመረዳት እንደሚቻል ጠቁመው "ከጠባብ ዓለም መውጣት ሲቻልም የመቻቻልና መግባባት ባህልን መፍጠር ይቻላል" ብለዋል።

የጋራ ምክክር መድረኩ በጋራ ዓላማ ዙሪያ በመሰባስባል በየወቅቱ መፈታት የሚገባቸውን ችግሮች በመለየት መስራት እንደሚያስችል አብራርተዋል።

"ኢትዮጵያዊያን አባቶቻችን ከ125 ዓመታት በፊት ያሳዩትን ገድል ዛሬም ልጆቻቸው ይደግሙታል" በማለት ወጣቶች አገራቸው ያላትን ሃብት ወደስራ መለወጥ እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የምክክር መድረኩ ተሳታፊዎች እንዳሉትም አድዋ የጽናት፣ የአንድነትና የመተባበር ተምሳሌት ነውና ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአንድነት ለሠላምና አብሮነቱ መቆም እንዳለበት መክረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም