"አድዋ የመተባበር፣ የመሰዋት፣ ከወገን በፊት ቀድሞ የመውደቅ መንፈስ ነው" -- ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል

84

የካቲት 20/2013 (ኢዜአ) አድዋ የዘር የበላይንትን፣ የኢ-ፍትሃዊነት መዋቅርን የሰበረ የነጻነትና የፍትህ ብርሃን ለጭቁኖች ያጎናፀፈ ድል ነው ሲሉ የሠላም ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል ተናገሩ።

"በስልጡን ምክክር አዲስ የተስፋ ምዕራፍ" በሚል መሪ ሃሳብ ብሔራዊ የልሂቃን የምክክር መድረክ በወዳጅነት አደባባይ እየተካሄደ ነው።

ብሔራዊ ምክክሩ ከክልል እስከ ቀበሌ በየደረጃው ለ6 ወራት ሲካሄድ መቆየቱ ተገልጿል፡፡

ለስድስት ወራት የተካሄደው ውይይት ፍሬያማ እንደነበርና ከቀበሌ እስከ ፌዴራል ያሉ ችግሮች ተነስተው ለተሻለ ተግባቦት የተሻለ ውጤት እንደተገኘበት ተመላክቷል።

ለቀጣይ መድረክ ወሳኝ መሰረት እንደሚጥልም ተነግሯል።

የሠላም ሚኒስቴርና ዴስቲኒ ኢትዮጵያ የምክክር መድረኩ አዘጋጆች ናቸው።

የሠላም ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል እንደገለጹት ላለፉት 6 ወራት ሲካሄድ የቆየውና በቀጣይም የሚጠናከረው መድረኩ ሰላማዊት፣ ዴሞክራሲያዊትና የበለጸገች ኢትዮጵያን በመገንባት ሂደት ልክ እንደ አድዋ ሁሉ ታሪካዊ ምዕራፍ ለመሆኑ ትልቅ ተስፋና እምነት የተጣለበት ነው።

የአድዋ ጦርነት ድል ብቻ ሳይሆን ኢ-ፍትሃዊ የዘር መድልዎ መዋቅርን የሰበረ የታሪክ ስር ስለመሆኑ ገልጸዋል።

የዓድዋ ድል አገር ያጸና፤ ከኢትዮጵያ አልፎ ለመላው ጥቁር ሕዝቦች ነጻነት ያመጣ ክስተትም ነው።

ሚኒስትሯ የዓለምን የፖለቲካና ማኅበራዊ መስመር የቀየሩ ሁነቶች፤ በይዘታቸውና በትምህርታዊ ፋይዳቸው የመጀመሪያ የሆኑ ክስተቶች ታሪካዊ መሆናቸውን አስረድተዋል።

አድዋ በኢትዮጵያዊያን የተመዘገበና ለዓለማችን ግፉዓን የነጻነትና የፍትህ ብርሃን የፈነጠቀ የኢትዮጵያዊያን የጋራ ታሪካዊ አሻራ እንደሆነም  አስገንዝበዋል።

አድዋ የሁለት አገራት ግጭት የወለደው ክስተት አለመሆኑን ገልጸው የሁለት ተጻራሪ ልዕለ ሃሳብ የጦርነት መነሻ መሆኑን ጠቁመዋል።

በጦርነቱ ኢትዮጵዊያን በአንድነትና በአሰባሳቢ ልዕለ ሃሳብ ድል መንሳታቸውን አውስተዋል ሚኒስትሯ።

ኢትዮጵያም በጦርቱ የነጻነትና የእኩልነትን ሃሳብ በታሪክ ብራናዋ በደማቁ ማስፈሯን ተናግረዋል።

አድዋ ኢትዮጵያ አሁን ላለችበት ምዕራፍ ትልቅ ትርጉም ስላለው ሁነቱን ለመዘከር የተፈለገበት መልካም አጋጣሚ እንደሆነም ገልጸዋል።

"ድሉም በጥቁር ሕዝቦች ታሪክ የኢትዮጵዊያን የመጀመሪያው፤ በውጤቱም የዓለምን ጨቋኝ መዋቅር የሰበረ ታሪካዊ አጋጣሚ ነው" ብለዋል።

ጥንታዊያን አባቶች ልዩነታቸውን በይደር ይዘው ለአንድ ዓላማ በአንድነት መሰለፋቸው ለድሉ መጎናጸፍ ሚናው ከፍተኛ እንደነበር አስታውሰዋል።

'አድዋ የመተባበር፣ የመሰዋት፣ ከወገን በፊት ቀድሞ የመውደቅ መንፈስ ነው' ሲሉ ነው የገለጹት፡፡

ሚኒስትር ሙፈሪያት "በእናቶችና አባቶች የቆመልንን አገር አንጥልም፤ የተሰቀለልንን ሰንደቅ አንዲት ስንዝር ዝቅ እንድትል አንፈቅድም" ነው ያሉት።

እየተካሄደ ባለው የምክክር መድረክ ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ ከ1 ሺህ 200 በላይ ሰዎች እየተሳተፉ ነው፡፡

መድረኩ ዛሬን ጨምሮ ለሶስት ቀናት የሚካሄድ ሲሆን እንደ አገር የሚነሱ የጋራ ችግሮችን በመለየት የጋራ መፍትሄ ማስቀመጥ እንደሚቻል ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም