በ169 ታዳጊዎች ላይ ሊፈፀም የነበረ ያለ እድሜ ጋብቻ እንዲቋረጥ ተደረገ

129

የካቲት 20 ቀን 2013 (ኢዜአ) በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር በ169 ታዳጊዎች ላይ ሊፈፀም የነበረ ያለ እድሜ ጋብቻ እንዲቋረጥ መደረጉን የዞኑ ሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች መምሪያ ገለጸ፡፡

በመምሪያው የሴቶች ግንዛቤ ንቅናቄ ባለሙያ አቶ በሪሁን ታመነ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ያለ እድሜ ጋብቻን ለማስቀረት ጋብቻ ከመፈፀሙ በፊት የእድሜ እና ተያያዥ ማስረጃዎችን የሚያረጋግጡ ሶስት ሆስፒታሎች አገልግሎት እየሰጡ ነው።

ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ ጋብቻ ለመፈፀም የእድሜ ምርመራ ካደረጉት 585 ጥንዶች ውስጥ 169 እድሜያቸው ለጋብቻ ያልደረሱ በመሆናቸው ጋብቻቸው እንዲቋረጥ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

ጋብቻ የተቋረጠባቸው ጥንዶች በስም ዝርዝር ተለይተው መያዛቸውንና በድብቅ ጋብቻ እንዳይፈፅሙ ከቀበሌ የፀጥታ አካላት እና ከትምህርት ቤቶች የጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ክበባት ጋር በመተባበር ክትትል እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በዚህ መሰረት በደረሰ ጥቆማ በዝቋላ ወረዳ ያለ እድሜ ጋብቻን በድብቅ ሊፈፅሙ የነበሩ ጥንዶችን ከትምህርት ቤቶች እና ከህብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ እንዲቋረጥ ተደርጎ ወላጆችም ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ መሆኑን ባለሙያው ጠቁመዋል።

ያለ እድሜ ጋብቻን ለማስቀረት ከሃይማኖት ተቋማት፣ ከፍትህ፣ ፖሊስ እና ትምህርት ቤቶች  እንዲሁም ከግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር  ጥምረት ተመስርቶ ለህብረተሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ እየተከናወነ መሆኑንም አመልክተዋል።

ከጋብቻ በፊት ምርመራ የሚያደርጉ ጥንዶች ቁጥር እየጨመረ ቢመጣም ድርጊቱን በሚፈለገው ልክ ማስቆም እንዳልተቻለ ጠቅሰው ህብረተሰቡ ያለ እድሜ ጋብቻን ለማስቆም ለሚደረገው ጥረት ተባባሪ ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም