ተቋሙ የቤተ-መጽሐፍቱን አገልግሎቶች የሚያስተዋውቅ አውደ ርዕይ ከፈተ

58

የካቲት 20/2013 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ቤተ-መጻሕፍት ለተጠቃሚዎች የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች የሚያስተዋውቅ አውደ ርዕይ ከፈተ።

የማስተዋወቂያ ዓውደ ርዕዩ ከዛሬ ጀምሮ እስከ የካቲት 24 ቀን 2013 ዓ.ም  ለሕዝብ ክፍት ይሆናል።

የአውደ ርዕዩ ዓላማ ቤተ-መጽሃፍቱ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች፣ የሰበሰባቸውንና ያዘጋጃቸውን በሌሎች ቤተ-መጽሃፍት የማይገኙ መረጃዎች የጥናትና ምርምር ባለሙያዎች እንዲጠቀሙ ለማስተዋወቅ ነው።

በ1955 ዓ.ም አስር ሺህ መጽሃፍት በማሰባሰብ የተቋቋመው ይህ ቤተ-መጻሕፍት አሁን 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን የታተሙና ያልታተሙ የሰነድ ክምችቶች እንዳሉት የተቋሙ ዳይሬክተር ዶክተር ታከለ መርዕድ ገልፀዋል።

ዶክተር ታከለ ቤተ-መጽሃፍቱ በአገር ውስጥና በዋና ዋና የዓለም ቋንቋዎች የተሰነዱ ክምችቶች እንዳሉት ተናግረዋል።

ቤተ-መጽሃፍቱ የጥናትና ምርምር መሆኑና ኢትዮጵያን የሚመለከቱ መረጃዎችን መያዙ ከሌሎች የተለየ እንደሚያደርገውም ገልፀዋል።

ለዚህ አብነት ሲጠቅሱም የዓባይን የጥናትና ምርምር ክፍተቶች ለመሙላት "የዓባይ ጓዳ" የሚሰኝ ክፍል እንደተዘጋጀለት ዶክተር ታከለ አስረድተዋል።

የተጠቃሚውን ፍላጎት ለመመለስ ከተቋቋመ ጀምሮ ያልተቋረጠ መረጃ በመሰብሰብ፣ ለተቋማት የስልጠናና የማማከር አገልግሎት በመስጠት ማኅበራዊ ሃላፊነቱን እየተወጣ ነው ብለዋል።

ቤተ-መጽሃፍቱ ለተጠቃሚዎቹ ዘመኑ የሚጠይቀውን አገልግሎት ለመስጠት የዲጂታላይዜሽንና የኦንላይን አገልግሎት እንዲሁም የራሱን ደንብና መመሪያ ማዘጋጀት ቀሪ ስራዎች አሉት ብለዋል ዶክተር ታከለ።

ለቀጣዩ ትውልድ ቅርሶችን ማቆየትና ማስተላለፍ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ነው ያሉት ደግሞ የቤተ መጽሃፍቱ ባለሙያ አቶ አሰፋ ወልደማርያም ናቸው።

ባለሙያው ቤተ-መጽሐፍቱ ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ ለአገልግሎት ክፍት የሆኑ የጥናትና ምርምር ማዕከል፣ የዓባይ ጉዳይን ለብቻ የያዘ የዓባይ ጓዳ፣ የዲጂታላይዜሽንና አውቶሜሽን ክፍል፣ የሥልጠናና የማማከር ክፍሎች እንዳሉት አብራርተዋል።

እስከ 2012 ዓ.ም ድረስ በገነተ ልዑል ቤተ-መንግስት ሙዚየም ውስጥ የነበረው ቤተ-መጽሃፍቱ ከሜድሮክ ግሩፕ በተገኘ 116 ሚሊዮን ብር ወደተገነባለት ህንፃ ተዛውሯል፡፡

ቤተ-መጻሕፍቱ በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ውስጥ ከሚገኙት የምርምር፣ የኢትኖግራፊ ሙዚየም፣ የኦዲዮ ቪዥዋልና የድህረ-ምረቃ ከሚባሉ አምስት የስራ ክፍሎች አንዱ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም