የህዳሴው ግድቡ ውሃው በሚተኛበት ስፍራ ሁለተኛ ዙር ምንጣሮ በመጪው መጋቢት ወር እንደሚጀመር ተገለጸ

74

አሶሳ ፤የካቲት 20/2013 (ኢዜአ) ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ውሃው በሚተኛበት ስፍራ ሁለተኛ ዙር የደን ምንጣሮ ስራ በመጪው መጋቢት ወር እንደሚጀመር የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቴክኒክና ሙያ ስራ እድል ፈጠራ ኢንተርፕራይዞች ኤጀንሲ ገለጸ፡፡

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ በሽር አብዱራሂም ለኢዜአ እንደተናገሩት  የህዳሴው ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት ስራ ለማስጀመር ውሃው በሚተኛበት ስፍራ የሚገኘውን አካባቢ ምንጣሮ ስራ የሚከናወነው ክልሉ  ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር ስምምነት በማድረግ ነው፡፡

ሁለተኛ ዙር የደን ምንጣሮ ከመጪው መጋቢት እስከ ሚያዚያ ወር  2013 ዓ.ም. እንደሚከናወን አስታውቀዋል፡፡

የደን ምንጣሮ ስራው ከግድቡ ግራ እና ቀኝ በኩል የሚገኙ በመተከል ዞን ሰዳል፣ ሸርቆሌ እና ወምበራ ወረዳዎች እንደሚከናወን የጠቆሙት አቶ በሽር አራት ሺህ 854 ሄክታር ይሸፍናል ብለዋል፡፡

ለደን ምንጣሮ ስራው 81 ሚሊዮን ብር መመደቡንም ገልጸዋል፡፡

ስራውን የሚያከናውኑ በ500 ኢንተርፕራይዞች የታቀፉ ከአምስት ሺህ በላይ የክልሉ ስራ አጥ ወጣቶች እንደሚሳተፉ ዋና ዳይሬክተሩ አመልክተዋል፡፡

ከባህር ጠለል በላይ ከ560 እስከ 595 ሜትር ከፍታ ላይ በሚከናወነውን የደን ምንጣሮ አንድ ኢንተርፕራይዝ እስከ 10 ሄክታር መሬት ይሸፍናል ብለዋል፡፡

የመተከል ዞን የጸጥታ ሁኔታ በየጊዜው መሻሻል እየታየበት እንደመጣ ያመለከቱት አቶ በሽር የደን ምንጣሮ ስራው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሚመራው የዞኑ ኮማንድ ፖስት ጋር በቅንጅት እንደሚከናወን አስረድተዋል፡፡

በመጀመሪያው ዙር ውሃ ሙሌት የአንድ ሺህ ሄክታር ደን ምንጣሮ የተከናወነው በክረምት ወራት እንደሆነ ያስታወሱት ዋና ዳይሬክተሩ ይህም በስራው ላይ ጫና አሳድሮ እንደነበር ተናግረዋል፡፡

ከዚሀ ተሞክሮ በመውሰድ የሁለተኛውን ዙር ደን ምንጣሮ ስራ ከወዲሁ እንዲጀመር ተወስኗል ብለዋል፡፡

የህዳሴው ግድብ ኢትዮጵያዊያን በአንድነተ  እየገነቡት ያለው ፕሮጀክት እንደሆነ የጠቆሞት አቶ በሽር የክልሉ መንግስት ስራውን በተቀመጠለት ጊዜ አጠናቆ ለማስረከብ በቁርጠኝነት እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የክልሉ ህዝብ በተለይ ወጣቱ የአካባቢውን ሠላም በመጠበቅ ለስራው ስኬት የድርሻውን እንዲወጣም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም