አክሱም ዩኒቨርሲቲ 2ሺህ 867 ተማሪዎችን አስመረቀ

114

መቀሌ፤ የካቲት 20/2013(ኢዜአ) አክሱም ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች በመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን 2ሺህ 867 ተማሪዎችን ዛሬ አስመረቀ፡፡

ተማሪዎቹ የተመረቁት በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ምትኩ ኃይሌ አዳራሽ ነው ፡፡

የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ገብረእየሱሰ ብርሃኔ በምርቃው ሥነ-ሥርዓት ወቅት እንደገለጹት ተመራቂዎቹ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት የተቋረጠውን የመጨረሻ ሴሚስተር ትምህርት ባለፉት ሶስት ወራት በመቀሌ ዩኒቨርስቲ እንዲያጠናቅቁ ተደርጓል፡፡

ከተመራቂዎቹ መካከል 2ሺህ 701 በመጀመሪያ ዲግሪ ቀሪዎቹ ደግሞ በሁለተኛ ዲግሪ የተማሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው የደረሰበትን ጉዳት አስተካክሎ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደነበረበት በመመለስ መደበኛ የመማር ማስተማሩ ሥራ እንደሚጀምርም ፕሮፌሰር ገብረእየሱሰ አስታውቀዋል፡፡

ከተመራቂ ተማሪዎች መካከል በመጀመሪያ ዲግሪ በነርስ የትምህርት ክፍል የተመረቀው አንዱ ዓለም ታመነ በሰጠው አስተያየት ከፍተኛ ውጣ ውረድ አልፈው ለምረቃ በመብቃቱ መደሰቱን ገልጿል።

የኮሮና ወረርሽኝና የጸጥታ ችግር በትምህርት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ቢያሳድርም ይህንን በማለፍ ለምረቃ መብቃታችን ደስተኛ ነኝ ያለችው ደግሞ በመጀመሪያ ዲግሪ የመካኒካል ኢንጅነሪንግ ተመራቂ ዜና ምንተስኖት ናት፡፡

አክሱም ዩኒቨርስቲ ሥራ ከጀመረበት ከ1999 ዓ.ም. ጀምሮ ለ12ኛ ጊዜ ማስመረቁን ከዩኒቨርሲቲው የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም