የጄኔራል ዊንጌትና የአዲስ አበባ ተግባረ-ዕድ ሳተላይት ካምፓሶች ተማሪዎችን አስመረቁ

92

የካቲት 20/2013 (ኢዜአ) የጄኔራል ዊንጌት እና የአዲስ አበባ ተግባረ-ዕድ ሳተላይት ካምፓሶች በመምህርነት ሙያ በመጀመሪያ ዲግሪ ያሰለጠኗቸውን 129 ተማሪዎች አስመረቁ፡፡

የአዲስ አበባ ተግባረ ዕድ ሳተላይት ካምፓስ 71፤ የጄኔራል ዊንጌት ሳተላይት ካምፓስ ደግሞ 58 ተማሪዎችን ነው ያስመረቁት፡፡

ምሩቃኑ በኮንስትራክሽን፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ በማኑፋክቸሪግና በጋርመንት የትምህርት መስኮች ለሦስት ዓመታት ትምህርታቸውን ሲከታተሉ ቆይተው በመጀመሪያ ዲግሪ ለምረቃ በቅተዋል።

የጄኔራል ዊንጌት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን አቶ መለስ ይመር ምሩቃኑ በትምህርት ቆይታቸው ያገኙትን እውቀት ወደ ተግባር በመቀየር ብቁና አገር የሚጠቅም ትውልድ ማፍራት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።

በአገሪቷ የኢንዱስትሪውን ዘርፍ ለማሳደግ እየተደረገ ያለውን ጥረት ውጤታማ ለማድረግ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና አሰልጣኞችን ደረጃ ማሳደግ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

በኢንተርፕራይዞች የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት በኮሌጁ ጥናትና ምርምር ከማካሄድ ባለፈ ምርታማ ሆነው ራሳቸውንና አገራቸውን እንዲጠቅሙ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

አገራዊውን የብልጽግና ጉዞ እውን ለማድረግ ምሩቃኑ በሰለጠኑበት የሥራ ዘርፍ በብቃትና በትጋት መስራት እንዳለባቸው ያሳሰቡት ደግሞ የአዲስ አበባ ተግባረ ዕድ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን አቶ ግሩም ግርማ ናቸው።

አገሪቷን ወደሚፈለገው የዕድገት ደረጃ ለማድረስ በስነ-ምግባር የታነፀ ትውልድ ከማፍራት ባሻገር ሁሉም ለሠላምና ለአንድነት የሚጠበቅበትን አስተዋጽኦ ማበርከት ይኖርበታል ብለዋል፡፡

ምሩቃኑ ወደሥራ ዓለም ሲገቡ አገራዊ አንድነትን የሚገነቡ እሴቶችን ተጠቅመው በማስተማር አገር ወዳድ ዜጋ ማፍራት እንዳለባቸውም አቶ ግሩም አሳስበዋል፡፡

የጄኔራል ዊንጌት እና የአዲስ አበባ ተግባረዕድ ኮሌጆች የተማረ የሰው ኃይል ለማፍራት ከዲፕሎማ እስከ ሦስተኛ ዲግሪ ለማስተማር ፍቃድ ማግኘታቸውን የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

በምረቃ ሥነ-ስርዓቱ ላይ የአዲስ አበባ አስተዳደር ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎችና የተመራቂዎች ቤተሰቦች ተገኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም