ኮሌጁ ሠራዊቱን በሙያ መገንባት የሚያስችል ስርዓተ ትምህርት ቀርጿል

407

የካቲት 20/2013 (ኢዜአ) በመከላከያ ዩኒቨርሲቲ የሪሶርስ ማኔጅመንት ኮሌጅ ሠራዊቱን በሙያ መገንባት የሚያስችል ስርዓተ ትምህርት መቅረጹን አስታወቀ።

በቀረጸው ስርዓተ ትምህርት ላይ ግብዓት ለማሰባሰብ የሚያስችል መድረክም አካሂዷል። 

በመድረኩ ምሁራን፣ የሠራዊቱ ከፍተኛ መኮንኖችና በስርዓተ ትምህርት ቀረጻ ሂደት የተሳተፉ አካላት ታድመዋል።    

በመከላከያ ዩኒቨርሲቲ የሪሶርስ ማኔጅመንት ኮሌጅ አካዳሚክ ዲን አቶ አይችሉህም ከተማ መከላከያ ሠራዊት ግዳጁን በተሟላ መልኩ እንዲፈጽም ሙያዊ አቅሙን ማሳደግ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

በዩኒቨርሲቲው የሚሰጠው ትምህርት ከሠራዊቱ ተልዕኮና ኃላፊነት ጋር የተጣጣመ እንዲሆን በሚያስችል መልኩ ስርዓተ ትምህርት መቀረጹን አስታወቀዋል።   

እንደ ዲኑ ገለጻ ኮሌጁ በአካውንቲንግና ፋይናንስ፣ በማኔጅመንት፣ በሎጂስቲክስና ሰፕላይ ቼን ማኔጅመንት፣ በጋዜጠኝነትና ተግባቦት እንዲሁም በሕግ ትምህርት ዘርፎች ስርዓተ ትምህርት ቀርጿል።  

በየትምህርት መስኩ የመከላከያን ፍላጎት መሰረት ያደረጉ ሀሳቦች በስርዓተ ትምህርቱ እንዲካተቱ መደረጉን ጠቅሰው ይህም ሠራዊቱን በተሻለ ሙያ የሚያጠናክርና ግዳጁን በአግባቡ ለመወጣት የሚያግዝ ነው ብለዋል።     

በመደበኛ ከሚሰጠው ትምህርት ጎን ለጎን የውትድርና ስነ ምግባር፣ የውትድርና ስነልቦና፣ ውትድርና እና ሕግ የመሳሰሉትም በአዲስ መልክ ተቀርጸው በስርዓተ ትምህርቱ መካተታቸውን አብራርተዋል።

መከላከያ ሳይስተጓጎል ሥራውን እንዲከውን መሰል የማሻሻያ ሥራዎች ፋይዳ እንዳላቸው ነው አቶ አይችሉህም የገለፁት።   

በመከላከያ ዩኒቨርሲቲ የሪሶርስ ማኔጅመንት ኮሌጅ አዛዣ ኮሎኔል ደሳለኝ አስፋው በበኩላቸው ኮሌጁ ችግር ፈቺ ምርምር በማካሄድ ለሲቪል ማኅበረሰቡ የሚተርፍ ተግባር እያከናወነ መሆኑን ገልፀዋል።

የምርምር ሥራ ጥራትን የጠበቀ መሆን እንዳለበት አመልክተው አሁን የተደረገው የስርዓተ ትምህርት ቀረጻ ይሄን ጉዳይ ከግምት ያስገባ መሆኑን ገልጸዋል።      

በመከላከያ ዩኒቨርሲቲ የሪሶርስ ማኔጅመንት ኮሌጅ በዓመት እስከ 500 ተማሪዎችን ለመቀበል አቅዶ እየሰራ እንደሚገኝ ከኮሌጁ የተገኘው መረጃ ይጠቁሟል።