በትግራይ የወባ በሽታ የመከላከል ስራ እየተካሄደ ነው

94
መቀሌ ሀምሌ 20/2010 በትግራይ ክልል የክረምቱ መግባት ተከትሎ ሊከሰት የሚችለውን  የወባ በሽታ ለመከላከል  የኬሚካል ርጭትና የአልጋ አጎበር ስርጭት እየተካሄደ ነው። በክልሉ ጤና ቢሮ የበሽታዎች ክትትልና ቁጥጥር ቡድን አስተባባሪ አቶ ዮሐንስ ገብረሃዋሪያት እንደገለጹት፣ከትግራይ አካባቢዎች 75 በመቶ በየዓመቱ ክረምትን ተከትሎ ለወባ በሽታ ተጋላጭ ናቸው። በክልሉ ጤና ቢሮ፣ባለድርሻ አካላትና ህብረተሰብ በሚያደርጉት የተቀናጀ የመከላከልና የቁጥጥር ስራ በሽታውን በወረርሽኝ የመከሰቱ አጋጣሚ እየቀነሰ መጥቷል። ዘንድሮም በሽታውን በወረርሽኝ መልክ እንዳይከሰት አስቀድሞ ለመከላከል እንዲቻል የአገልግሎት ዘመናቸው ያጠናቀቁ  ከ1 ሚሊዮን 900 ሺህ በላይ የአልጋ አጎበሮችን በአዲስ እንዲተኩ ለ34 ወረዳዎች ተሰራጭቷል፡፡ የተሰራጩት አዳዲስ የአልጋ አጎበሮችም በወረዳዎቹ በበሽታው ምክንያት ይጠቃል ተብሎ የሚገመተውን 3 ሚሊዮን 500 ሺህ የሚጠጋ ህዝብ ከበሽታው አስቀድሞ መታደግ  እንደሚቻል ነው አስተባባሪው ያመለከቱት። በክልሉ ለወባ ይበልጥ ተጋላጭ በሆኑ 20 ወረዳዎች የሚገኘው ህዝብ ከበሽታው ለመታደግም የመከላከያ ኬሚካል ርጭት የሚካሄድባቸው መሆኑን  አቶ ዮሐንስ አስረድተዋል። በኬሚካል ርጭት ወቅትም ከግማሽ ሚሊዮን በላይ መኖሪያ ቤቶችን የሚሸፍን እንቅስቃሴ የሚከናወን ሲሆን፣በቅርቡ ከ18 ሺህ ግሎግራም ኬሚካል ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ተልኮ የርጭት ስራ መጀመሩን ተናግረዋል። እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ2030 ክልሉን ከወባ በሽታ ሙሉ በሙሉ ነጻ ለማድረግ እየተሰራ ባለው ስራም ውጤት እየመጣ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም