በዘላቂ የኑሮ ዋስትናን ማረጋገጥ ፕሮግራም 230 ሺህ ቤተሰቦች ተጠቃሚ ሆኑ

59

ሀዋሳ ፤የካቲት 20/2013 (ኢዜአ) በአምስት ክልሎች በተመደበ ስምንት ሚሊዮን 500 ሺህ ብር ወጪ በተካሄደው ዘላቂ የኑሮ ዋስትናን ማረጋገጥ ፕሮግራም 230 ሺህ ቤተሰቦች ተጠቃሚ መሆናቸው ተገለጸ።

ባለፉት ሁለት ዓመታት በፕሮግራሙ የተከናወኑ ስራዎችን ለመገምገም የተዘጋጀው የምክክር መድረክ በሀዋሳ ከተማ እየተካሄደ ነው።

የፕሮግራሙ ብሄራዊ አስተባባሪ ዶክተር ቴዎድሮስ ተፈራ በመድረኩ እንደተናገሩት ፤ ከኔዘርላንድ መንግስት በተገኘ ገንዘብ የተካሄደው ፕሮግራሙ በትግራይ፣አማራ፣ደቡብ፣ ኦሮሚያና ሲዳማ ክልልች የምግብ ዋስትና እጥረት ባለባቸው 62 ወረዳዎች ውስጥ ነው።

በወረዳዎቹ በዓመት እስከ ዘጠኝ ወር ድረስ የምግብ እጥረት ያለባቸው ቤተሰቦች እንዳሉ በጥናት መረጋገጡን ያመለከቱት አስተባባሪው ይህንን ችግር ለማቃለል ፕሮግራሙ ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀሱን ተናግረዋል።

ፕሮግራሙ በክልሎቹ ከሚገኙ ስምንት ዩኒቨርስቲዎች፣ ግብርና ቢሮ፣የአደጋ ስጋት መከላከልና ስራ አመራር ኮሚሽንና ምርምር ተቋማት ጋር በአጋርነት መሰራቱን ገልጸዋል።

ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ በፕሮግራሙ አማካኝነት የምግብ እጥረት ችግርን ለመፍታት የሚያስችሉ ምርጥ የግብርና ተሞክሮዎች የመለየት፣የማላመድና የማስፋት ስራዎች መከናወናቸውን አመልክተዋል።

በዚህ ረገድ የተሻሻሉ የሰብል፣ጥራጥሬ፣ፍራፍሬ እና የስራስር ዘሮችን ለምግብ ዕጥረት ተጋላጭ ለሆኑ አርሶ አደሮች በማሰራጨት ተጠቃሚ ማድርግ መቻሉን አስረድተዋል።

እንዲሁም በአነስተኛ ማሳ ላይ ምርምር በማካሄድ 60 የሚጠጉ ምርታማነትንና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ውጤታማ ቴክኖሎጂዎችን የመለየት ስራ መከናወኑን አስታውቀዋል።

በህጻናትና እናቶች ላይ ጎልቶ የሚታየውን የሥርዓተ ምግብ ችግር ለማቃለልም ወጣቶችን በማደራጀት በቀላሉ የሚለሙ ፍራፍሬዎችን፣ የፕሮቲንና ቫይታሚን ኤ ይዘታቸው ከፍተኛ የሆኑ ሰብሎችን በማልማት ተደራሽ ተደርጓል ብለዋል።

በተለይ በአርሶ አደሮች፣ልማት ጣቢያ ሰራተኞችና ኤክሰፐርቶች ጋ የነበረውን የእውቀትና የክህሎት ክፍተት በስልጠና ለመሙላት ጥረት መደረጉንም አብራርተዋል።

በነዚህና ሌሎችም ስራዎች 230 ሺህ ቤተሰቦች ተጠቃሚ መሆናቸውን ዶክተር ቴዎድሮስ አስታውቀዋል።

የመንግስት ፖሊሰን ከማስፈጸም አንፃር የነበሩ ክፍተቶችን የመሙላት ስራም በፕሮግራሙ መከናወኑን ጠቁመው መድረኩም የተዘጋጀው በፕሮግራሙ ከተከናወኑት ውስጥ የትኞቹ ውጤታማ ስራዎች ወደ መንግስት ይሸጋገሩ የሚለውን ለመመለስ ነው ብለዋል።

ለሶስት ዓመት የተቀረጸው ይኸው ፕሮግራም ሊጠናቀቅ ሶስት ወራት እንደሚቀሩት ከአስተባባሪው ገለጻ ለመረዳት ተችሏል።

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር አያኖ በራሶ በሰጡት አስተያየት ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር በክላስተር በመተሳሰር በደቡብና ሲዳማ ክልሎች በሚገኙ 10 ወረዳዎችና 40 ቀበሌዎች ውስጥ በፕሮግራሙ አማካኝነት ውጤታማ ስራ መከናወኑን ተናግረዋል።

በወረዳዎቹ የሴፍቲኔት ተጠቃሚ አርሶ አደሮች በምግብ ሰብል ራሳቸውን እንዲችሉ ምርታማ የግብርና ቴክኖሎጂዎች የማሰራጨትና የማላመድ ተግባራት መፈጸማቸውንም አስረድተዋል።

ፕሮግራሙ ለምግብ ዕጥረት ተጋላጭ የሆኑትን አርሶ አደሮች ከመደገፍና ከማብቃት አንፃር ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ዶክተር አያኖ አረጋግጠዋል።

ለሁለት ቀናት በተዘጋጀው መድረክ ከግብርና ሚኒስቴር፣ ደቡብና ሲዳማ ክልሎች ግብርና ምርምር ተቋማት፣ከሀዋሳና አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ የፕሮግራሙ አስተባባሪዎችና ባለሙያዎች እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም