“ብሔራዊ ምክክር ማድረግ ብሔራዊ መግባባት ላይ ለመድረስ ያለን አማራጭ ነው” ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ

65

የካቲት 20/2013 (ኢዜአ) በሰላም ለመኖርና የምንፈልገው እድገት ለማሳካት ብሔራዊ ምክክር በማድረግ ብሔራዊ መግባባት ላይ ከመድረስ ውጭ ሌላ አመራጭ ሊኖር እንደማይችል የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ ገለጹ።

በአንድነት ፓርክ “በስልጡን ምክክር አዲስ የተስፋ ምዕራፍ” መርሐግብር እየተካሄደ ነው።

በመርሐግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት ፕሬዚዳንት ሠኅለወርቅ ዘውዴ ይህ የምክክር መድረክ 125ኛው የአድዋ ድል በዓል በኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ባሉበት የአለም ክፍል ሁሉ በከፍተኛ ሁኔታ እየተከበረ ባለበት ወቅት መካሄዱ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።

የአድዋ ድል ለጋራ አላማ የአንድ አገር ህዝብ ልዩነቶቹን በመተው እንዴት በአንድነት መቆም እንደሚቻል ያሳዩበት ብቻ ሳይሆን አገርን ከወራሪ ለመከላከል ውድ ሕይወትን በመሰዋት ያስተማሩበት ነው ብለዋል።

የአድዋ ድል ያለ ዘር፣ ሐይማኖት እና የአካባቢ ልዩነት እንደተገኘ ሁሉ በዚህ ዘመንም ከአድዋ በመማር ያለ ልዩነት መቆም ይገባል ብለዋል።

“ለማንኛውም ስራችን የአድዋ መንፈስን መላበስ አለብን፣ ኢትዮጵያውያን በአገረ ግንበታ ላይ ምን ሚና አለኝ ብለን እያንዳንዳችን ልንሰራ ይገባል” ነው ያሉት።

“በሰላም ለመኖርና ለማደግ ብሔራዊ ምክክር በማድረግ ብሔራዊ መግባባት ላይ ከመድረስ ሌላ ምን አማራጭ አለን’ ሲሉም ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

ብሔራዊ ምክክር ማድረግ ድርድር አይደለም፣ እርቅ መፈለግ አይደለም የመወያየትና የመግባባት መድረክ ነው’፣ መፍትሔ የሚገኘው ከመወያየትና ከመግባባት ይህም ለሀገር ጽኑ መሰረት ይጥላል” በማለት አስገንዝበዋል።

በጋራ ስንገናኝ ሌላውን ለመረዳት እንችላለን ያሉት ፕሬዚዳንቷ “ከጠባብ አለም ስንወጣ ነው መቻቻልን መግባባትን የምንፈጥረው” ብለዋል።

ለምክክር በአንድ ጥላ ስር መሰባሰብ በራሱ ትልቅ እርምጃ መሆኑን ጠቁመው በባህላችን ውስጥ ያሉ ችግር መፍቻዎችን በመፈተሽ ልንማርባቸው ይገባል በማለት አመልክተዋል።

የጋራ ምክክር መድረክ በአለማ ዙሪያ ያሰባስባል ስለዚህም በየወቅቱ መፍታት የምንችላቸውን ነገሮች እየለየን መስራት ይኖርብናል ሲሉ አመልክተዋል።

ኢትዮጵያውያን አባቶቻችን ከ125 ዓመታት በፊት ያሳዩትን ገድል ዛሬም ልጆቻቸው ይደግሙታል ያሉት ፕሬዚዳንቷ ወጣቶች ሀገራችን ያላትን ሃብት ወደ ስራ ሊለውጡት ይገባልም ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም