የአዲስ አበባና ፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን ነዋሪዎችን ግንኙነት ለማጠናከር ይሰራል - ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ

112

የካቲት 19/2013 (ኢዜአ) የአዲስ አበባና ፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን ነዋሪዎችን ግንኙነት ለማጠናከር በትኩረት እንደሚሰራ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

በፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን የትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብር በይፋ ተጀምሯል።

ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ዛሬ በሰንዳፋ ከተማ ተገኝተው መርሃ ግብሩን አስጀምረዋል።   

በስነ-ስርዓቱ ላይ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ፣ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ጃንጥራር አባይና የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ቶላ በሪሶ ተገኝተዋል።  

መርሃ ግብሩ ተግባራዊ የተደረገው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለፈው ዓመት በዞኑ የተማሪዎች ምገባ መርሃ ግብር ለማስጀመር ቃል በገባው መሰረት መሆኑ ተገልጿል።

ለ161 ሺህ ተማሪዎች ተደራሽ የሚሆነው የትምህርት ቤት ምገባው ለአንድ ዓመት የሚካሄድ ሲሆን 669 ሚሊዮን ብር በጀት ተይዞለታል።

ከቅድመ መደበኛ እስከ 12ኛ ክፍል ያሉት ተማሪዎቹ ከምገባው በተጨማሪ የትምህርት ቁሳቁስና የደንብ ልብስ እንደሚያገኙም ተገልጿል።

የአዲስ አበባና የፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን ነዋሪዎች ወንድማማቾች መሆናቸውን የተናገሩት ምክትል ከንቲባዋ ጥቂት ግለሰቦች ለጥቅማቸው ብለው ልዩነትና መጠራጠርን ሲሰብኩ መቆየታቸውን አስታውሰውል።

የአዲስ አበባ ሕዝብ ለፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን ነዋሪዎች ልዩ ክብር እንዳለው በመግለጽ 'ከመሬት በፊት ሕዝብ ይቀድማል፤ ሕዝብ ተያይዞ ነው ማደግ ያለበት' ብለዋል።

በአካባቢዎቹ ነዋሪዎች መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር በትኩረት እንደሚሰራ የተናገሩት ምክትል ከንቲባዋ ዛሬ በትምህርት የተጀመረው ትብብር ወደ ሌሎች መስኮችም እንደሚሰፋ አመልክተዋል።

"የአዲስ አበባ ሕዝብና የፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን አንድ ሕዝብ ነው" ያሉት ደግሞ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ ናቸው።

የለውጥ አመራሩ የነበረውን ክፍተት በመለየት የሁለቱን ሕዝቦች ትስስር ለማጠናከር እየሰራ መሆኑንና ይህም አዲስ ምዕራፍ መክፈቱን ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከራሱ ባለፈ በፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን የተማሪዎች ምገባ መርሃ ግብር ማስጀመሩ የሚያስመሰግን ተግባር ነው ብለዋል።

ለተማሪዎች ምገባ የተደረገው ድጋፍ ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ የጎላ ሚና ስላለው መምህራንና ተማሪዎች ለዚሁ ስኬት የድርሻቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ተማሪዎች በበኩላቸው ባገኙት ድጋፍ መደሰታቸውንና ድጋፉ በቀጣይ ትምህርታቸውን በተነቃቃ መንፈስ ለመከታተል እንደሚረዳቸው ተናግረዋል።  

በምግብ እጥረት ምክንያት ትምህርታቸውን በአግባቡ መከታተል የሚቸገሩ ተማሪዎች እንደነበሩ አስታውሰው የምገባ መርሃ ግብሩ ችግሩን እንደሚያቃልለው እምነታቸውን ገልፀዋል።

ተማሪ ትንቢት አየለ፣ ተማሪ ቤተልሄም ታሪኩ እና ተማሪ ቤተልሄም በዳሳ፡-

በመርሃ ግብሩ ይፋ ማድረጊያ ስነ ስርዓት የፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን ለምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤና በዕለቱ ለተገኙ ከፍተኛ አመራሮች ፈረስና ባሕላዊ አልባሳት በሽልማት አበርክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም