በትግራይ ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የዕለት ደራሽ ድጋፍ እየተደረገ ነው-ኮሚሽኑ

59

ሶዶ የካቲት 19 ቀን 2013 (ኢዜአ) በትግራይ ለ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎች የዕለት ደራሽ ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎች እየተደረገ መሆኑን የብሄራዊ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

በክልሉ በነበረው ህግ ማስከበር ዘመቻ ጋር ተያይዞ አንዳንድ የውጭ መገናኛ ብዙሃን የእርዳታ ፈላጊዎችን ቁጥር 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን አድርገው መዘገባቸው በተገቢ መረጃ ያልተደገፈና ስህተት መሆኑን ኮሚሽኑ ገልጻል።

ከሚሽኑ የበጀት አመቱን የስድስት ወር የስራ አፈጻጸም ከትላንተ ጀምሮ በወላይታ ሶዶ ከተማ እየገመገመ ነው።

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ ለኢዜአ እንደገለጹት በተግራይ ክልል ተፈጽሞ በነበረው ሃገር የመካድ ተግባር ለማረም በተወሰደው ህግ የማስከበርና የህልውና ዘመቻ ምክንያት ባንክ ቤቶችና ሌሎች የንግድ ተቋማት በቂ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ እንዳልነበር አስታውሰዋል፡፡

 በክልሉ  በወቅቱ ለመንግስት ሠራተኛው ደመወዝ ያልተከፈለበትና በህገ ወጥ ቡድኖች ምክንያት የተፈጸሙ ዘረፋዎችና መሰል ጫናዎች ስለነበሩ ሁኔታዎቹን  ከግምት በማስገባት 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎች ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል በሚል ግምታዊ መረጃ ወጥቶ እንደነበር ገልጸዋል፡፡

ኮሚሽኑ ባደረገው የዳሰሳ ጥናት መነሻ ከህግ የማስከበር ዘመቻው በፊት 1 ነጥብ 8 ሚሊየን እንዲሁም ከህግ ማስከበር ዘመቻ በኃላ 700 ሺህ ዜጎች እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው መታወቁን ተናግረዋል።

በክልሉ ባጠቃላይ ለ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎችን የመደገፍ ሥራዎች ለማከናወን የታቀደ ቢሆንም ኮሚሽኑ ካለው ቁጥር ከፍ አድርጎ በማቀድ ለ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎች የዕለት ደራሽ ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎች እያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል ።

ለወገኖቹ እየተደረገ ካለው ድጋፍ ውስጥ 70 በመቶው በመግስት ቀሪው ደግሞ ከተለየዩ ተራድኦ ድርጅቶች የተገኘ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በትግራይ ክልል የሚደረገው ድጋፍ ፍላጎቱ እስካለ ድረስ በተጠናከረ መልኩ የሚቀጥል መሆኑን አመላክተዋል።

እስከአሁን እየተላከ ያለው እርዳታ ለታለመለት ዓላማ እየዋለ መሆኑንና አለመሆኑን ለማረጋገጥና የቀጣይ የድጋፍ ተግባራትን ለማጠናከር ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ የሁለተኛ ዙር ዳሰሳ ጥናት የሚያደርግ ቡድን ወደ ክልሉ እንደሚንቀሳቀስ ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል ።

በጉዳዩ ዙሪ ከሚመለከታቸው አካላት በቂ መረጃ ሳይኖራቸው ዘገባ የሚያወጡ የመገናኛ ብዙሃን ሊታረሙ እንደሚገባ  ኮሚሽነሩ አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም