በወልድያና አካባቢዋ በ15 ቀናት ውስጥ 76 ሰዎች በእብድ ውሻ ተነከሱ

78

የካቲት 19 ቀን 2013 (ኢዜአ) በወልድያ ከተማና አካባቢው በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ በእብድ ውሻ የተነከሱ 76 ሰዎች ለህክምና መምጣታቸውን የወልድያ ሆስፒታል አስታወቀ።

የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ሞገስ በርየ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ በአካባቢው የእብድ ውሻ በሽታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ መጥቷል።

በእብድ ውሻ ከተነከሱት መካከል ስድስቱ ህጻናት መሆናቸውን ገልጸው፤ ከአንድ ዓመት ህፃን እስከ 82 ዓመት አዛውንት መጎዳታቸውን ተናግረዋል።

ከአጠቃላይ ተጎጅዎች መካከል 68ቱ ከወልድያ ከተማ እንዲሁም 8ቱ ከሰሜን ወሎ ከአምስት ወረዳዎች የመጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ከተጎጅዎቹ መካከል ለ21ዱ ህሙማን በሆስፒታሉ ህክምና እንደተሰጣቸ የገለጹት ዶክተር ሞገስ፤ በሆስፒታሉ ባለው የመድሃኒት አቅርቦት እጥረት ምክንያት ቀሪዎቹ ወደ ደሴ ሆስፒታል ተልከው ህክምና እንዲያገኙ መደረጉን አመልክተዋል።

በ15 ቀናት ውስጥ 76 ሰዎች በእብድ ውሻ መነከሳቸው ችግሩ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን እንደሚያመላክትም ገልጸዋል።

ማንኛውም የእብድ ውሻ ተጠቂ ግለሰብ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ክትባትና ህክምና ማግኘት እንዳለበት ጠቁመው፤ "ይህ ካልሆነ ለሞት የሚያጋልጥ አደገኛ በሽታ ነው" ብለዋል።

በንክሻ የቆሰለውን አካልም ወዲያውኑ በሳሙናና ውሃ ማጠብና ወደ ጤና ተቋም ፈጥኖ መሄድ እንደሚያስፈልግ መክረዋል።

የወልድያ ከተማ አስተዳደር ጤና ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሞላ ካሳው በበኩላቸው በከተማውና አካባቢው የእብድ ውሻ በሽታ እየተስፋፋ መምጣቱን አረጋግጠው፤ "ባለቤት አልባ ውሾች መበራከት የችግሩ ምንጭ ነው" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም