ጉምሩክ ኮሚሽን 4 ሺህ 320 ኪሎ ግራም አደንዛዥ እጽ በቁጥጥር ስር አዋለ

113

የካቲት 19 ቀን 2013 (ኢዜአ) "ኤፍኤስአር" በተሰኘ ተሽከርካሪ ተጭኖ ከሻሻመኔ ወደ ሞያሌ ሲጓጓዝ የነበረ 4 ሺህ 320 ኪሎ ግራም አደንዛዥ እጽ በቁጥጥር ስር ማዋሉን የጉምሩክ ኮሚሽን ገለጸ።

የአደንዛዥ እጹ ግምታዊ ዋጋ ከ17 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሆነም ተገልጿል።

በኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ሀዋሳ ቅርንጫፍ የጪጩ መቆጣጠሪያ ጣቢያ አስተባባሪ ኮማንደር ጫላ ቡልቻ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ትናንት በቁጥጥር ስር የዋለውን አደንዛዥ እጽ ሲያጓጉዝ የነበረው አሽከርካሪ በቁጥጥር ስር ውሏል።

የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3-23878 አ.አ በሆነ ኤፍ ኤስ አር የጭነት ተሽከርካሪ ሲጓጓዝ የነበረው አደንዛዥ እጽ ከሻሻመኔ ወደ ሞያሌ እየተጓዘ እንደነበር ተናግረዋል።

መቆጣጠሪያ ጣቢያው ጥቆማ ደርሶት ክትትል ሲያደረግ መቆየቱን ያወሱት አስተባባሪው፤ አሽከርካሪው የሰሌዳ ቁጥሩን በመቀየር አጭበርብሮ ለማለፍ ሙከራ ማድረጉን አስረድተዋል።

ባለፉት ስድስት ወራት ከ88 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ እቃዎች በቁጥጥር ስር ያዋለው ጣቢያው፤ የአሁኑን ጨምሮ ባለፉት ከ8 ሺህ ኪሎ ግራም በላይ አደንዛዥ እጽ በቁጥጥር ስር እንዳዋለ አስታውሰዋል።

ከአስፓልት ውጭ በጫካና ውስጥ ለውስጥ መንገዶች በመጠቀም የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ ቢኖርም ከጸጥታ አካላትና አካባቢው ማህበረሰብ ጋር በመስራት ድርጊቱን ለማስቆም ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ኮማንደር ጫላ አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም