ለምርጫው ስኬታማነት የድርሻቸውን እንደሚወጡ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሴቶች ሊግ አባላት ገለጹ

48

አሶሳ ፤ የካቲት 19/ 2013( ኢዜአ) ስድስተኛው ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ የተሳካና የሴቶች ተሳትፎ እንዲጠናከር የድርሻቸውን እንደሚወጡ የብልጽግና ፓርቲ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሴቶች ሊግ አባላት ገለጹ፡፡

"የሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለሁለንተናዊ ብልጽግና "በሚል ለሊጉ አባላት የንቅናቄ መድረክ ዛሬ በአሶሳ ከተማ ተካሄዷል፡፡

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የሊጉ አባል ወይዘሮ መሠረት በጂዲዳ በተለይ ለኢዜአ እንዳሉት ብልጽግና ፓርቲ በፓርላማ እና በሚኒስትር ደረጃ ለሴቶች ተሳትፎ መጠናከር ትኩረት ሰጥቷል፡፡

ይሁንና ብዙ ሴቶች በታችኛው የአስተዳደር እርከን አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ጠቁመው በሚኒስትር ደረጃ የተገኘውን የሴቶች የአመራነት ተሳትፎ ከክልል እስከ ቀበሌ ማውረድ ይቀረናል ብለዋል፡፡

በክልሉ የሴቶች ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ምቹ ሁኔታዎች እየሰፉ መምጣታቸወን የተናገሩት ወይዘሮ መሰረት መጪው ምርጫ የተሰካና ለሴቶች ህይወት መሻሻል አስተዋጽኦ እንዲኖሮው  መስራት አለብን ብለዋል፡፡

ሌላው የሊጉ አባል ወይዘሮ ፋጡማ መሀመድ በበኩላቸው በክልሉ ብቃት እያላቸው የአመራርነት እድል ያላገኙ በርካታ ሴቶች እንዳሉ ገልጸዋል፡፡

እንኚህን ሴቶች ወደ ሃላፊነት ማምጣት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

በክልሉ መጪው ምርጫ ሠላማዊ ቢሆን ዋነኛ ተጠቃሚ ሴቶች እንደሚሆኑ ገልጸው የሊጉን አደረጃጀት ለምርጫው ስኬታማነት ድርሻው የጎላ ሆኖ መገኘት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

ሊጉ የክልሉ ሴቶች ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ አቅም እንዲዳብር ወሳኝ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ያስረዱት ደግሞ  ወይዘሮ ሙሉ ወርቁ ናቸው፡፡

ይህ እንዲቀጥል የታችኛውን የሊጉን አደረጃጀት ማጠናከርን ትኩረት አድርገን እየሠራን ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የብልጽግና ፓርቲ የክልሉ ሴቶች ሊግ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ ስንታየሁ አበበ  በስድስተኛው ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ በክልሉ  174 ሺህ ያህል ሴቶች በመራጭት እንደሚሳተፉ  እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡

ከለውጡ በፊት በክልሉ በአስፈጻሚውም ሆነ ሌሎች ዘርፎች የሴቶች ተሳትፎ ዝቅተኛ እንደነበር አውስተው  አሁን መሻሻል እየታየበት መምጣቱን ጠቁመዋል፡፡

ሴቶች በምርጫው ሲሳተፉ ይበጀኛል የሚለውን ፓርቲ በሚገባ መለየት ፤  ለዚህ ደግሞ ከወዲሁ አንባቢ እና ምክንያታዊ ሆነው ውሳኔ ላይ መድረስ አለባቸው ብለዋል፡፡

አብዛኛው ሴቶች ደግሞ ይህን በማድረግ ምርጫው ተአማኒ እንዲሆን የድርሻቸውን መወጣት እንደሚችሉ እምነታቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም