በጎንደር ከተማ የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት 10 ሚሊዮን ብር ተመድቦ እየተሰራ ነው

45

ጎንደር ፤የካቲት 18/2013(ኢዜአ) በጎንደር ከተማ የሚስተዋለውን የኑሮ ውድነትና የዋጋ ንረትን በማረጋጋት ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ የግብርና ምርቶችን ለማቅረብ 10 ሚሊዮን ብር ተመድቦ ወደ ስራ መገባቱን የከተማዋ አስተዳደር አስታወቁ፡፡

አስተዳደሩ በከተማዋ ከተቋቋሙ የሸማቾች ኅብረት ስራ ማህበራትና ዩንየኖች አመራሮች ጋር ዋጋ በማረጋጋት ረገድ የድርሻቸውን መወጣት በሚችሉበት ዙሪያ ዛሬ ተወያይቷል፡፡

በውይይት መድረኩ የአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባው አቶ ተሾመ አግማስ እንደተናገሩት፤ በከተማው ከቅርብ ግዜ ወዲህ የተከሰተውን የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት ለመቀነስ የገበያ አረጋጊ ግብረ ሃይል በማቋቋም ወደ ስራ ተገብቷል፡፡

ከተማ አስተዳደሩ በከተማው ዋጋ በማረጋጋት ስራ ለተሰማራው የዳሽን የሸማቾች ህብረት ስራ ዩንየን ለግብርና ምርቶች ግዢ የሚያውለው ከወለድ ነጻ 10 ሚሊዮን ብር በብድር መስጠቱን ገልጸዋል፡፡

በከተማው በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችና ለ49 የመንግስት መስሪያ ቤቶች ሰራተኞች ጤፍና ሩዝ በተመጣጣኝ ዋጋ የማቅረብ ስራ መጀመሩን የገለጹት የዳሽን ሸማቾች ህብረት ስራ ዩንየን ስራ አስኪጅ ወይዘሮ አድና አለምዬ ናቸው፡፡

ከተማ አስተዳደሩ ለዩንየኑ ከመደበው 10 ሚሊዮን ብር ውስጥ በግማሹ 1ሺ 100 ኩንታል ጤፍና 100 ኩንታል ሩዝ በመግዛት ማከፋፈል መጀመራቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ዩንየኑ የግብርና ምርቶቹን በስሩ በሚገኙ 11 የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት አማካኝነት እያሰራጨ እንደሚገኝ፤ በተለይ ጤፍ ከገበያ ዋጋ በኩንታል እስከ 300 ብር ቅናሽ ባለው ዋጋ እየሸጠ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የአዘዞ አየር ማረፊያ የሸማቾች መሰረታዊ ማህበር ጸሃፊ መምህር አካል ወርቁ 1ሺ 325 ለሚሆኑ የማህበሩ አባላት 500 ኩንታል ቀይ ጤፍ ከገበያ ዋጋ 300 ብር ቅናሽ በማድረግ ኩንታሉን በ3ሺህ 300 ብር ለህብረተሰቡ እንደተሰራጨ ተናግረዋል።

የከተማዋ አስተዳደር ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ሃላፊ አቶ አደራጀው አላበ በበኩላቸው ጤናማ የንግድ እንቅስቃሴና የተረጋጋ የገበያ እንዲኖት ለማስቻል የተጠናከረ የክትትልና ቁጥጥር ስርዓት መዘርጋታቸውን ገልጸዋል።

ሰው ሰራሽ የምርት አቅርቦት እጥረትና የዋጋ ንረት በመፍጠር ሸማቹ እንዲማረርና ገበያው እንዳይረጋጋ ህገ ወጥ የንግድ ስራ ሲያከናውኑ በተገኙ 40 የእህል መጋዘኖች እንዲታሸጉ መደረጉን ጠቅሰዋል።

ከተፈቀደላቸው የንግድ ቦታ ውጭ አየር በአየርና በተሸከርካሪ ላይ የሚነግዱ ነጋዴዎችንም በመቆጣጠር የማስተካከያ እርምጃ እንደተወሰደም ተናግረዋል፡፡

በከተማው የሚገኙ የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራትና ዩንየኖችም አስተዳደሩ በመደበው ገንዘብ አስፈላጊውን የግብርና ግብአቶች በተመጣጣኝ ዋጋ ገዝተው ለነዋሪው በወቅቱ እንዲያቀርቡ አሳስበዋል፡፤

በውይይት መድረኩ በከተማዋ የሚገኙ ሁለት ዩንየኖችና 19 መሰረታዊ የሸማቾች ኅብረት ስራ ማህበራት አመራሮች ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም