የጣይቱ የባህልና ትምህርት ማዕከል በኢትዮጵያ ስራ ሊጀምር ነው

100

አዲስ አበባ፤ የካቲት 18/2013(ኢዜአ) የጣይቱ የባህልና ትምህርት ማዕከል በኢትዮጵያ ስራ መጀመር የሚያስችለውን ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አስታወቀ።

ማዕከሉ በአዲስ አበባ ለስራ ማከናወኛ የወሰደውን የቅርስ ቤት እድሳት ለመጀመር መጋቢት 4 ቀን 2013 ዓ.ም ያዘጋጀውን የትውውቅና የገቢ ማሳባሰቢያ መርሃ ግብር አስመልክቶ ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

የጣይቱ የባህልና ትምህርት ማዕከል በነሐሴ 1993 ዓ.ም በሰሜን አሜሪካ ዋሺንግተን ዲሲ በኢትዮጵያዊያንና በትውልደ ኢትዮጵያዊያን የተቋቋመ ነው።

ማዕከሉ በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የአገራቸውን ባህል ፣ታሪክ ፣ ቋንቋና ኪነጥበብ እንዲያውቁ የውይይት መድረኮችን በመፍጠር፣በማሰልጠንና በማቀራረብ ላይ ሲሰራ ቆይቷል።

የጣይቱ የባህልና ትምህርት ማዕከል ስራ አስኪያጅና የኪነ ጥበብ ባለሙያ ዓለምጸሐይ ወዳጆ፤ ማዕከሉ በውጭ አገራት ያገኘውን ልምድና እውቀት በአገር ውስጥ ለማስፋት ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል።

ማዕከሉ በኢትዮጵያ ስራ ለመጀመር ለመንግስት ባቀረበው ጥያቄ መሰረት ሕዳር 3 ቀን 2011 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቢትወደድ ሃይለጊዮርጊስ ወልደሚካኤል መኖሪያ ቤት የነበረውን በቅርስነት የተመዘገበ ቤት አድሶ እንዲገለገልበት መረከቡን አስታውሰዋል።

መኖሪያ ቤቱ 117 ዓመታት ማስቆጠሩንና ከዳግማዊ ምኒልክ ሐውልት አጠገብ የቀድሞ የአራዳ ምድብ ችሎት ግቢ ውስጥ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

ማዕከሉ መኖሪያ ቤቱን ከተረከበ በኋላ ቅርስነቱን እንደጠበቀ አስጠግኖ ለመገልገል ቤቱን ለማደስ ሲያስጠናና ከቦታው ጋር የሚጣጣም የማስፋፋያ ዲዛይን ሲሰራ ቆይቷል ብለዋል።

በተደረገው ጥናት ለመኖሪያ ቤቱ ከ15 እስከ 20 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደሚያስፈልግና ማዕከሉ የተጠቀሰውን ያህል ወጪ በራሱ አቅም መሸፈን የሚችል ባለመሆኑ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሩን ማዘጋጀቱን ነው የማዕከሉ ስራ አስኪያጅ የገለጹት።

በመጀመሪያ ምዕራፍ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብርና ማዕከሉ የሌሎች የገቢ ማሰባሰቢያ አማራጮችን ተጠቅሞ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ እድሳቱን አጠናቆ ወደ ስራ ለመግባት እቅድ መያዙን ጠቁመዋል።

ከመኖሪያ ቤቱ የቀድሞ የአራዳ ምድብ ችሎት ግቢ ያሉትን ሕንጻዎች አድሶ ለገቢ ማመንጫነት ለመጠቀም እንደሚፈልግና ለዚህም ከ50 እስከ 60 ሚሊዮን ብር ገንዘብ እንደሚያስፈልገው አመልክተዋል።

የጣይቱ የባህልና ትምህርት ማዕከል በኢትዮጵያ ስራ ሲጀምር የኪነጥበብ የስነ ጥበብ ባለሙያዎች ስራቸውን የሚያቀርቡበትና ሌሎች የኢትዮጵያ ባህል ኪነ ጥበብ ስራዎች የሚደግፉ ተግባራት እንደሚከናወኑ ተናግረዋል።

ሁሉም ባህልና ኪነጥበብ ወዳድ ኢትዮጵያዊ ማዕከሉ የሚያከናውነውን ስራ እንዲደግፍ ጥሪ አቅርበዋል።

የጣይቱ የባህልና ትምህርት ማዕከል የቦርድ አባል ጋዜጠኛ ሄኖክ ቴዎድሮስ በበኩሉ መጋቢት 4 ቀን 2013 ዓ.ም በሚካሄደው የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር የኪነ ጥበብ ስራዎችን ለጨረታ ማቅረብ ጨምሮ የተለያዩ የገቢ ማስገኛ ኩነቶች እንደሚካሄዱ አመልክቷል።

በገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሩ የመንግስት ባለስልጣናት፣መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ታዋቂ ግለሰቦችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ይገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ በመግለጫው ወቅት ተገልጿል።

በታዋቂዋ የኪነጥበብ ባለሙያ ዓለምፀሐይ ወዳጆ ፋና ወጊነት በግጥም ንባብ በ1993 ዓ.ም ስራ የጀመረው የጣይቱ የባህልና ትምህርት ማዕከል በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን ከባህላቸውና ከታሪካቸው ጋር እንዲገናኙ በማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳደረገ ይነገራል።

ማዕከሉ በርካታ የስነ ጽሁፍ ምሽቶችን በማዘጋጀት እንዲሁም አትሮችን አዘጋጅቶ በተለያዩ አገራት የማቅረብ ስራ አከናውኗል።

በስነ-ግጥም፣ በቋንቋ፣ በቴያትር ዝግጅት፣ በትወና፣ በፊልም ስራ፣ በመገናኛ ብዙሃንና በፈጠራ ጽሑፍ ላይ ያተኮሩ አውደ ጥናቶችን በማዘጋጀት የእውቀትና የልምድ ልውውጥ መድረኮችን ፈጥሯል።

በተጨማሪም ማዕከሉ በዋሺንግተን ዲሲ ውስጥ በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነ ለኢትዮጵያዊያን አገልግሎት የሚሰጥ የንባብ ቤትም አቋቁሟል።

ማዕከሉ ላለፉት 20 ዓመታት ላበረከተው አስተዋጽኦ ከ50 በላይ ሽልማቶችንና የምስክር ወረቀቶችን አግኝቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም