ከስደት ለተመለሱ ዜጎች 13 ባለ ሶስት እግር ተሽከርካሪዎች ተበረከቱ

305

አዲስ አበባ፣ የካቲት 18 /2013 ዓ.ም (ኢዜአ)  የስደትና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ ከተለያዩ የአውሮጳ አገራት ለተመለሱ ወገኖች የ13 ባለ ሶስት እግር ተሽከርካሪዎች ቁልፍ አስረከበ።

ድጋፉ የተደረገው ከአውሮፓ ኅብረት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ መሆኑን የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ ገልጸዋል።

ድጋፍ የተደረገላቸው ከስደት ተመላሾች በተለያዩ ጊዜያት በሕገ ወጥ መንገድ አውሮፓ ገብተው በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩና ወደ አገራቸው የተመለሱ ናቸው ብለዋል።

እነዚህ ዜጎች ከአማራ፣ ከኦሮሚያ፣ ከአዲስ አበባ፣ ከሶማሌና ከሲዳማ ክልሎች የተውጣጡ ሲሆኑ ሶስቱ ሴቶች ናቸው።

አቶ ተስፋሁን ከስደት ተመላሾቹ በተደረገላቸው እገዛ ለሌሎች ተመላሾች አርዓያ የሚሆን ስራ መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በአውሮፓ ኅብረት የኢትዮጵያ ፕሮግራም ኦፊሰር አንጄሎ ዲ. ጆርጂ በበኩላቸው ኅብረቱ የገንዘብ ድጋፉን ያደረገው በተለያዩ የአውሮፓ አገራት በአስቸጋሪ ሁኔታ ወስጥ የነበሩና የተመለሱ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም መንግስት እያደረገ ያለውን ጥረት ለመደገፍ ነው ብለዋል።

በተለያዩ የአውሮፓ አገራት በችግር ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን መኖራቸውንና ችግሩ እስኪቀረፍ ድረስ ኅብረቱ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

መንግስት ስደትን በማስቀረት ዜጎች በአገራቸው ሰርተው እንዲኖሩ ለማድረግ እያደረገ ያለውን ጥረት እንደሚያደንቁ ከስደት ተመላሾቹ ተናግረዋል።

በቀጣይ በተሰማሩበት የስራ መስክ ውጤታማ በመሆን ለሌሎች የስራ ዕድል በመፍጠር ስደትን ለማስቀረት ለሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን እንደሚወጡ ገልፀዋል።