ከግብርና ወደ ኢንቨስትመንት ለተሸጋገሩ አርሶ አደሮች የስራ እድል ፈጠራ ስልጠና እየተሰጠ ነው- ቢሮው

82

ነቀምቴ፣ የካቲት 18/2013 /ኢዜአ/ ከግብርና ወደ ኢንቨስትመንት ለተሸጋገሩ ግንባር ቀደም አርሶ አደሮች በስራ እድል ፈጠራ ሥልጠና መስጠት መጀመሩን የኦሮሚያ የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ አስታወቀ።

በቢሮው የኢንቨስትመንት ሽግግር ባለሙያ አቶ ዳዊት አስፋው ለኢዜአ እንደገለጹት ከአራቱ የወለጋ ዞኖች ለተወጣጡና ወደ ኢንቨስትመንት ለተሸጋገሩ ግንባር ቀደም አርሶ አደሮች የተዘጋጀ  የሶስት ቀን ስልጠና ዛሬ በነቀምቴ ከተማ ተጀምራል ።

ስልጠናው  በስራ እድል ፈጠራ፣ በንብረና ገንዘብ አያያዝና አጠቃቀም ላይ ያተኮረ መሆኑን ተናግረዋል ።

የኦሮሚያ ቴክኒክና ሙያ ቢሮ ሃላፊና የሥልጠናው አስተባባሪ አቶ ኤባ ገርባ በበኩላቸው አራቱ የወለጋ ዞኖች በተፈጥሮ ሀብት የታደሉና  ክረምት ከበጋ የሚፈሱ በርካታ ወንዞች ያሏቸው መሆናቸውን ተናግረዋል።

አርሶ አደሩ በአካባቢው ያለውን ሀብት በመጠቀም በዓመት ሁለቴና ከዚያ በላይ በማምረት የምግብ ዋስትናውን ከማረጋገጥ ባሻገር በገበያ ተፈላጊ የሆኑ ምርቶችን በማምረት ገቢውን ማሳደግ እንደሚገባው አስገንዝበዋል ።

እርሻውንም ከተለመደ አሰራር ወደ ተሻሻለ አስተራረስ በማሸጋገር ግብርናውን ለማዘመን መትጋት እንዳለበት አመላክተዋል።

ወደ ኢንቨስትመንት የተሸጋገሩ አርሶ አደሮችም ከሥልጠናው የሚያገኙትን ግንዛቤ ወደ ተግባር በመቀየር የኢንቨስትመንት ሥራቸውን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሳደግ ጠንክረው መስራት እንዳለባቸው መክረዋል።

በሥልጠናው ከምሥራቅ፣ ከምእራብ፣ ከሆሮ ጉዱሩና ከቄለም ወለጋ ዞኖች የተውጣጡ 700 ሞዴል አርሶ አደሮች እየተሳተፉ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም