ለፋብሪካ ግብዓት የሚውል ከ234 ሺህ ኩንታል በላይ የጥጥ ምርት ተሰበሰበ

74

መተማ ፣ የካቲት 18/2013 (ኢዜአ) በምዕራብ ጎንደር ዞን ለፋብሪካ ግብዓት የሚውል ከ234 ሺህ ኩንታል በላይ የጥጥ ምርት መሰብሰቡን የዞኑ ግብርናና ገጠር ልማት መምሪያ አስታወቀ፡፡

በመምሪያው የሰብል ልማት ቡድን መሪ አቶ ቻላቸው አቸነፍ እንደተናገሩት የጥጥ ምርቱ የተሰበሰበው በ2012/13 የምርት ዘመን ከለማው 20ሺህ 900 ሄክታር መሬት ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የተሰበሰበው በዘመኑ ይገኛል ተብሎ ከታቀደው 400 ሺህ ኩንታል የሚጠጋ ምርት ውስጥ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

''በእቅድ የተቀመጠውን ያህል ማግኘት ያልተቻለውም በፀጥታ ችግር የጥጥ ምርቱ መለቀም ባለበት ሰዓት መሰብሰብ ባለመቻሉ የባከነ ምርት በመኖሩ ነው'' ብለዋል።

ይህም ሆኖ የተገኘው ጥጥ ጥራት ያለው ምርት በመሆኑ አርሶ አደሩና ባለሃብቱ በጥሩ ዋጋ እየሸጡ ተጠቃሚ እያደረጋቸው መሆኑን አሰረድተዋል።

በጥጥ ልማቱ ከ11 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችና ባለሃብቶች መሳተፋቸውን ጠቅሰው የጥጥ ምርቱ የተገኘው በዞኑ ቋራ፣ ምዕራብ አርማጭሆ እና መተማ ወረዳዎች ውስጥ መሆኑን ገልጸዋል።

በአካባቢው የጥጥ መዳመጫ ፋብሪካ መኖሩ አርሶ አደሩ በልማቱ በስፋት እንዲሳተፍ እድል ፈጥሯል ብለዋል።

በምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ በ20 ሄክታር መሬት ጥጥ በማልማት 130 ኩንታል ምርት ማግኘት እንደቻሉ የገለጹት ደግሞ ባለሀብት የሆኑት አቶ ጋሻው አዲሱ ናቸው።

''የዘንድሮው ምርት ጥራት ያለውና በተሻለ ዋጋ የሚሸጥ በመሆኑ ተጠቃሚ ነኝ'' ያሉት ባለሃብቱ አንዱን ኩንታል በ3 ሺህ 500 ብር ሂሳብ እየሸጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

እስካሁንም 100 ኩንታሉን በመሸጥ ከ350 ሺህ ብር በላይ ገቢ እንዳገኙ ጠቅሰዋል።

ከዚህ በፊት የጥጥ ምርት ገበያ ላይ ብዙም ስለማይሸጥ ምርቱም ለብልሽት ባለሃብቱም ለኪሳራ ይዳረግ እንደነበር ያስታወሱት ባለሃብቱ አሁን ዋጋው መሻሻሉ በቀጣይ በሰፊው እንዲያመርቱ የሚያነሳሳ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ሌላኛው በመተማ ወረዳ የሽመለ ጋራ ቀበሌ አርሶ አደር አወቀ ሲሳይ በበኩላቸው በጥጥ ካለሙት አምስት ሄክታር መሬት ላይ 54 ኩንታል ምርት መሰብሰባቸውን ተናግረዋል፡፡

''በዋጋ ደረጃ ባለፈው ዓመት ከነበረው በዕጥፍ ተሸሽሏል'' ያሉት አርሶ አደሩ ካመረቱት የጥጥ ምርት ከወጪ ቀሪ ከ100 ሺህ ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውንም ገልጸዋል፡፡

በምዕራብ ጎንደር ዞን ባለፈው ዓመት ከ17 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ከለማው ጥጥ 280 ሺህ ኩንታል ምርት መገኘቱን ከግብርናና ገጠር ልማት መምሪያው የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም