ምርጫው ነጻ፣ ተአማኒና ተቀባይነት ያለው እንዲሆን እየተሰራ ነው- የአማራ ብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት

99

ባህርዳር፣ የካቲት 18/2013 (ኢዜአ) 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ነጻ፣ ተአማኒና በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያለው እንዲሆን እየተሰራ መሆኑን የአማራ ብልፅግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

የጽሕፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ አብረሃም አለኽኝ ለኢዜአ እንደገለጹት በሀገሪቱ ከዚህ ቀደም የተካሄዱ አምስት ምርጫዎች በሀሳብ ደረጃ ዴሞክራሲያዊና ሁሉን አቀፍ ተቀባይነት ያላቸው ሲሆኑ በተግባር ግን ተግዳሮት የነበረባቸውና ለይስሙላ የተካሄዱ ነበሩ ።

"የዘንድሮ 6ኛው አገራዊና ክልላዊ  ምርጫ  የኢትዮጰያውያን መጻኢ ተስፋን ግብ አድርጎ የሚካሄድ በመሆኑ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል" ብለዋል ።

"የዘንድሮ ምርጫ በለውጡ ማግስት የሚካሄድ በመሆኑ  ህጎች የተሻሻሉበትና የዴሞክራሲ ተቋማት እራሳቸውን ችለው እንዲቆሙ የተደረገበት መሆኑንም ልዩ ያደርገዋል" ሲሉ ተናግረዋል።

ምርጫው በእውነታ ላይ የተመሰረተ ነጻ፣ ገለልተኛ፣ ተአማኒና በመራጩ ህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያለው እንዲሆን እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸው በብልጽግናና በተፎካካሪ ፓርቲዎች ዘንድ መተማመን ያለበት ሆኖ እንዲካሄድ በመሰራት ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

ብልፅግና ፓርቲን በመወከል ከአማራ ክልል ለህዝብ ተወካዮችና ክልል ምክር ቤቶች የሚወዳደሩ እጩዎች የመመልመልና የምርጫ ምልክቱንና ማኒፌስቶ የማስተዋወቅ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አመልክተዋል ።

"ምርጫው ሃገረ መንግስትን ለመገንባት ወሳኝ ነው'' ያሉት አቶ አብረሃም ለምርጫው ስኬታማነት ተባብሮና ተደጋግፎ መስራት የግድ መሆኑን ገልጸዋል።

ብልፅግና ፓርቲ በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር የመግባቢያ ሰነድ በመፈራረም ጭምር ስራዎችን በጋራ የመስራት እንቅስቃሴ መጀመሩን ሀላፊው ተናግረዋል።

የመጭው ጊዜ ብሩህነት በዚህ ታሪካዊ ምርጫ ይወሰናል'' ያሉት ሃላፊው በቅድመ ምርጫ፣ በምርጫና በድህረ ምርጫ ወቅት የሚሰሩ ጠንካራ ስራዎች የምርጫውን ተአማኒነት ጉልህ እንደሚያደርጉት ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

እስከ ምርጫው ያሉ እንቅስቃሴዎች ህግና ስነ ምግባርን የተከተሉ መሆን እንዳለባቸው ጠቅሰው "ለምርጫው ሂደት ሁላችንም ተደማሪ ችግር ሳይሆን ተደማሪ መፍትሄ መሆን ይገባል" ሲሉ አብራርተዋል።

በምርጫው ጤናማ ውድድር መደረግ እንዳለበት አመልክተው ብልፅግና ለዚህ ምርጫ ብዙ አማራጭ ፖሊሲዎችን ይዞ መቅረቡን አስረድተዋል።

"ብልፅግና ከነባራዊ ሁኔታ ጋር የተስማማ ዓለም አቀፍ ፖለቲካው የተግባባና ተዋህዶ መሬት ሊነካ የሚችል አማራጮችን ይዞ ቀርቧል" ብለዋል።

"ብልፅግና ወሰን አልባ የፖለቲካ አስተሳሰብ በማራመድ በሃገርና ህዝብ እድገት ላይ ተመሰርቶ ከአለም አቀፍ ፖለቲካ አሰላለፍ የሚጠቅመውን በመውሰድ የሚሰራ ነው" ሲሉም ተናግረዋል።

ፓርቲው የሃገርን የወደፊት እጣ ፈንታ በማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች የእለት ከእለት ግምገማ ላይ ተመስርቶ ብይን ሚሰጥ እንደሆነም አቶ አብረሃም አመልክተዋል።

"ፓርቲው እንደ አብዮታዊ ዴሞራሲ በመቃብሬ ላይ የሚል ቀይ መስመር የተሰመረበትና የማይለወጥ፣ የማይሻሻልና የማይቀየር የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም አለኝ ብሎ አያምንም" ሲሉ ገልፀዋል።

ምርጫው  ውጤታማና ስኬታማ  እንዲሆን እርስ በእርስ ተግባብቶ መስራት አማራጭ የሌለው በመሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላትና ተፎካካሪ ፓርቲዎች በሃላፊነት መንፈስ መስራት እንደሚገባም አቶ አብረሃም አስገንዝበዋል።

ብልፅግናም የምርጫው ተወዳዳሪ ቢሆንም ገዥው ፓርቲ በመሆኑ ለምርጫው ውጤታማነት የሚጠበቅበትን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም