በትግራይ ከ800 ኩንታል በላይ የእርዳታ እህል በህገ-ወጥ መንገድ ወጥቶ ሊጓጓዝ ሲል በቁጥጥር ስር ዋለ

69

ሽሬ፣ የካቲት 18/ 2013 ዓ.ም (ኢዜአ) የፌዴራል መንግስት ለሽሬ ከተማ እና አካባቢዋ ነዋሪዎች ዕርዳታ እንዲውል የላከው ከ800 ኩንታል በላይ እህል በህገ-ወጥ መንገድ ወጥቶ ሊጓጓዝ ሲል በቁጥጥር ስር መዋሉን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሽሬ ከተማ የጸጥታ ስምሪት አስታወቀ፡፡


ህገ-ወጥ ድርጊቱ ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው የተጠረጠሩ 10 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገልጿል፡፡

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሽሬ ከተማ የጸጥታ ስምሪት ሃላፊ ሻለቃ አብርሃም አረሩ እንደገለጹት ለመከላከያ ሃይሉ በተሰጠው ጥቆማ መሰረት ለህዝቡ እንዲውል የተላከው እህል በህገ-ወጥ መንገድ ተጭኖ ወደ ሌላ ቦታ ሊጓጓዝ ሲል ተይዟል፡፡

ከወንጀሉ ጋር የተጠረጠሩ ሰባት ግለሰቦችንና ሶስት አሽከርካሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ሻለቃ አብርሃም ጠቁመዋል፡፡

መንግስት ለህብረተሰቡ የላከው ሰብዓዊ ድጋፍ በትክክል መድረስ አለበት ያሉት ሻለቃው ተረጂዎች የወሰዱትን እህል ለፍጆታ መጠቀም እንጂ አውጥተው መሸጥ የለባቸውም ብለዋል፡፡  

በብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የሽሬና አካባቢዋ የሰብዓዊ ድጋፍ አስተባባሪ አቶ ታዬ ጌታቸው በበኩላቸው ለህብረተሰቡ የሚቀርበውን ሰብዓዊ ድጋፍ ማንም ሰው ወደተለያዩ ቦታዎች ማጓጓዝ አይችልም ብለዋል፡፡

የህብረተሰቡን ሃብት ባልታወቀ ሁኔታ ለሌላ ዓላማ ሊያውሉ የሞከሩ ግለሰቦች በህግ እንዲቀጡም ጠይቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም