የባቢሌ ዝሆኖች መጠለያ ፓርክ ከተጋረጠበት አደጋ ለመታደግ የተጀመሩ ስራዎች ማጠናከር እንደሚገባ ተጠቆመ

86

ሐረር ፤ የካቲት 18/ 2013(ኢዜአ) በኦሮሚያ ምሰራቅ ሐረርጌ ዞን እና ሱማሌ ክልል መካከል የሚገኘው የባቢሌ ዝሆኖች መጠለያ ፓርክ ከተጋረጠበት አደጋ ለመታደግ የተጀመሩ ስራዎች ማጠናከር እንደሚገባ ተጠቆመ።

ኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ባለስልጣን፣ የምስራቅ ዞን ሐረርጌና ሱማሌ ክልል አመራሮች መጠለያው ያለበትን ሁኔታ በስፍራው በመገኘት ትናንት ተመልክተዋል።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኩመላ ዋቅጅራ በወቅቱ እንደተናገሩት፤ የባቢሌ ዝሆኖች መጠለያ ፓርክ በህገ ወጥ ግንባታ፣እርሻ ስራና ሌሎች ሰው ሰራሽ ችግሮች ለአደጋ ተጋልጧል።

በዚህም ምክንያት በፓርኩ ውስጥ የሚገኙት ዝሆኖች በቂ ቦታ ስለሌላቸው በድንጋይ ላይ ቆመው መመልከታቸውንና  እየሞቱም መሆናቸውንም መረዳት እንደቻሉ ተናግረዋል።

ዝሆኖች የሚኖሩበት ስፍራ በመጣበቡ  ወደ እርሻ ማሳ በመግባት በሰዎች ላይ ጉዳት እንደሚያደርሱ ገልጸዋል።

በሁለቱም ክልል በኩል ያየናቸው ህገ ወጥ ቤት ግንባታን የማፍረስ፣ከእርሻና እንስሳታ ግጦሽ ነጻ የማድረግ ጅምር ስራዎች ቢኖሩም ችግሮቹን በዘለቂነት ለመፍታት በአካባቢው የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማሳመን ሀብቱን ከጉዳት የመጠበቁ ስራ  ማጠናከር ይገባል ብለዋል።

ባለስልጣኑ በሁለቱ ክልሎች ኮሚቴ አዋቅሮ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው በተለይ በቀጣይ ስራዎች ላይ ፓርኩንና ዝሆኖችን ለመታደግ የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ማዘጋጀቱንም አስታውቀዋል።

በምስራቅ ሐረርጌ ዞን የባቢሌ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ኢሊሞ በከር በበኩላቸው በባቢሌ፣ፈዲስና ሚደጋ ቶላ አካባቢዎች  የሚገኙ 4ሺህ አባወራዎችን በማወያየት በፓርኩ ዙሪያ የተገነቡ 4ሺህ መኖሪያ ቤቶችን በፍቃደኝነት ማፍረስ ተችሏል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት መጠለያው በሚገኝበት ሁለቱ ክልሎች መካከል ተመሳሳይ እርምጃ ባለመወሰዱ ህገ ወጥ ግንባታው ተመልሶ መቀጠሉን የጠቆሙት አስተዳዳሪው  በቀጣይ ስራው በቅንጅት መከናወን እንዳለበት  ተናግረዋል።

በሱማሌ ክልል የባቢሌ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ሙሰደድ ሃጂአብዲ ለአምስት ቀናት በተካሄደው እንቅስቃሴ በመጠለያ ፓርኩ ይኖሩ የነበሩ ከ1ሺህ በላይ  አባወራዎች የማስወጣት ስራ መከናወኑን ገልጸዋል።

ሆኖም በአንድ አካባቢ የሚኖሩ አርብቶ አደሮች ተመልሰው ሰፍረው መገኘታቸውን ጠቁመው እነዚህንም አወያይተው በማግባባት በአጭር ጊዜ የማስወጣት ስራ ይከናወናል ብለዋል።

የባቢሌ ዝሆኖች መጠለያ ፓርክ በ1970ዎቹ ከተቋቋሙት የዱር እንስሳ ጥበቃ ማዕከላት አንዱ ነው።

በሱማሌ ክልልና ኦሮሚያ ምስራቅ ሐረርጌ  ዞን አስር ወረዳዎች ባሉ  43 ቀበሌ ገበሬ ማህበራት ውስጥ  በሚገኘው መጠለያው ፓርክ  ውስጥ ዝሆኖቹ ይንቀሳቀሳሉ።

ሆኖም በህገ ወጥ መንገድ የሚከናወነው ሰፈራ ፣እርሻ ፣ ደን ጥፍጨፋና ቤት ግንባታ ምክንያት  የመጠለያ ፓርኩ ህልውና አሳሳቢ መሆኑ ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም