ማእከሉ ያባዛውን 200 ኩንታል ምርጥ የቡና ዘር ለስርጭት አዘጋጀ

99

ጅማ፣የካቲት 17/2013 (ኢዜአ)  የጅማ ግብርና ምርምር ማእከል ከኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ጋር በመተባበር ያባዛውን 200 ኩንታል ምርጥ የቡና ዘር ለስርጭት ማዘጋጀቱን አስታወቀ።

ማእከሉ በተጨማሪም ዝርያቸው የተሻሻለ 500 ሺህ የቡና ችግኞችን ለስርጭት ማዘጋጀቱን ለኢዜአ ገልጿል።

የጅማ ግብርና ምርምር ማእከል ዳይሬክተር ዶክተር ግርማ ሃይለሚካኤል እንደገለጹት ማእከሉ ከዚህ ቀደም በምርምር ያገኛቸውን የቡና ዝርያዎች በዘርና በችግኝ መልክ አባዝቶ ለአርሶ አደሮች ለማሰራጨት ዝግጁ አድርጓል።

የቡና ዝርያዎቹ በሀገሪቱ ቡና አብቃይ በሆኑ አካባቢዎች አየር ጠባይ ጋር የተላመዱና ምርታማነትን የሚጨምሩ መሆናቸውን ተናግረዋል ።

ለስርጭት የተዘጋጀው 200 ኩንታል ምርጥ የቡና ዘር 20ሺህ ሄክታር መሬት የማልማት አቅም እንዳለው ተናግረዋል ።

በተመሳሳይ በሚሰራጩት 500ሺህ የቡና ችግኞች 200 ሄክታር መሬት እንደሚለማ አመላክተዋል ።

ማእከሉ ከቡናና  ሻይ ባለስልጣን ጋር በመተባበር እየሰራ መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ "አርሶ አደሩ ቡናን ጥራቱን ጠብቆ እንዲያመርት በሚደረገው ጥረት ባለስልጣኑ ተገቢውን እገዛ እያደረገ ነው" ብለዋል፡፡

ማእከሉ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ በመረጣና በማዳቀል ምርምር ያገኛቸውን 42 የቡና ዝርያዎች  ለተጠቃሚ  በማድረስ  ለዘርፉ ምርትና ምርታማነት እድገት አስተዋጾ ማድረጉን ተናግረዋል።

ከቡና ዝርያዎቹ መካከል 35ቱ በመረጣና 7ቱ በማዳቀል የተገኙ መሆኑን ገልጸዋል ።

"በመረጣና በማዳቀል የተገኙት የቡና ዝርያዎች ከነባሩ ጋር ሲነጻጸሩ ከአምስት እጥፍ በላይ የምርት ጭማሪ አላቸው" ብለዋል።

ከማእከሉ የሚወጡ የቡና ዝርያዎች የተፈለገውን ምርት ይሰጡ ዘንድ ከተከላ ጀምሮ እስከ ምርት ስብሰባ ባለው ሂደት አርሶ አደሩ ተገቢውን የአሰራር ዘዴ መከተል እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ በማእከሉና በባለስልጣኑ ትብብር የተባዛውን ምርጥ የቡና ዘርና ችግኝ በሁሉም ቡና አብቃይ አካባቢዎች ለሚገኙ አርሶ አደሮች ለማሰራጨት ዝግጅት ተጠናቋል።

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ዳይሬክተር ዶከተር አዱኛ ደበላ በበኩላቸው "የቡናን የምርት መጠንና የጥራት ደረጃ ለማሻሻል አርሶ አደሩን በባለሙያ ማገዝ ተገቢ ነው" ብለዋል ።

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በኢትዮጵያ ቡና በብዛት እንዲመረትና በጥራትም ደረጃውን የጠበቀ ይሆን ዘንድ ከምርምር ማእከላት ጋር በትብብር እንደሚሰራ አመላክተዋል፡፡

"ኢትዮጵያ ካላት የቡና ማሳ አንጻር የሚገኘው ምርት በቂ አይደለም "ያሉት ዳይሬክተሩ በየአመቱ የሚሰበሰበው ምርት በጥራቱ ተወዳዳሪ መሆን እንዲችል በቅንጅት መስራት አስፈላጊ መሆኑን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም