በኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ላይ ተገንብቶ የቆየው የመጀመሪያው የጥላቻ ግንብ ተንዷል- ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ

116
አዲስ አበባ 19/2010 በኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን መካከል ተገንብቶ የቆየው የጥላቻ ግንብ መናዱን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገለጹ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት በአሜሪካ ዋሺንግተን ዲሲ እየተካሄደ ባለው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን የሚገኙ ሁለት ሲኖዶሶች መካከል ያለውን አለመግባባት ለመፍታት የተዘጋጀው የሰላም ማብሰሪያ ጉባኤ ላይ ነው። ዶክተር አብይ እንዳሉት የዛሬው ጉባኤ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ላይ ተገንብቶ የቆየው የመጀመሪያው የጥላቻ ግንብ መናዱን በይፋ የሚያበስር ነው። የዚህ ግንብ መፍረስ የሚያመላክተው በፖለቲካ፣ በዘርና በተለያየ ጥቅማ ጥቅም ልዩነቱን ያሰፉት ጉዳዮች መናድ ጭምር ነው ብለዋል። ሁላችንም በጋራ ተባብረን ፖለቲካችን፣ ሃይማኖታችን፣ ብሔራችን፣ ቋንቋችንና ኢትዮጵያዊነታችን በአንድ ጥላ ስር እንደሚታይ ተስፋ አለኝ ብለዋል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን ራሷን ከማስታረቅ አልፋ ኢትዮጵያን ወደ አንድነትና የመደመር ጉዞ በማምራት እየተካሄደ ባለው ጥረት የበኩሏን ስራ እንደምታከናውንም እምነታቸው እንደሆነ ተናግረዋል። በቀጣይ የሁለቱ ሲኖዶሶች የሰላም ማብሰሪያ ጉባኤም በሚሊኒየም አዳራሽ እንደሚካሄድ አመልክተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በእርቀ ሰላሙ ሂደት አስተዋጽኦ ላደረጉት አካላትም ምስጋናቸውን  አቅርበዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዋሽንግተን ዳላስ አየር ማረፊያ ሲደርሱም በአሜሪካ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር አምባሳደር ካሳ ተክለብርሃንን ጨምሮ በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሎስ አንጀለስና በዋሽንግተን ዲ ሲ በሚኖራቸው ቆይታም ከኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር ይወያያሉ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም