የተከበሩ የዓለም ሎሬት ዶክተር ጥበበ የማነብርሃን ስርዓተ ቀብር ተፈጸመ

134

የካቲት 16 ቀን 2013 (ኢዜአ) የተከበሩ የዓለም ሎሬት ዶክተር ጥበበ የማነብርሃን ስርዓተ ቀብር በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ቤተ-ክርስቲያን ተፈጸመ።

በሥርዓተ ቀብሩ ላይ ከፍተኛ የመንግስት ባለሥልጣናት፣ ወዳጅ ዘመዶቻቸውና ቤተሰቦቻቸው ተገኝተዋል።

እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ዶክተር ጥበበ የማነ ብርሃን በተለያዩ መስኮች ካበረከቱት አስተዋኦ መካከልም በአገሪቷ ሰላምና ወንድማማችነት እንዲጎለብት በኢትዮጵያ እርቀ ሰላም ኮሚሽን በኩል የሰሩት ስራ አንዱ ነው።

በላየንስ ክለብ ለረጅም ዓመታት የሰጡት አገልግሎት፣ በቀይ መስቀል ማህበርና በኢትዮጵያ ስካውት ማህበር በኩል አገር ወዳድ ወጣት እንዲፈራ በማድረግ ረገድ በርካታ ስራዎችን ሰርተው ያለፉ ናቸው።

ሎሬቱ የኢትዮጵያ እርቀ ሰላም ኮሚሽን ከተቋቋመ ጀምሮ ዓላማዎቹ እንዲሳኩ ያላሰለሰ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል።

በተለይም ኮሚሽኑ እንዲጠናከር ከአጋር አካላት ጋር ቅንጅቶች እንዲፈጠሩ ጥረት ሲያደርጉና በኮሚሽኑ አቅም ግንባታ ቋሚ ኮሚቴ በኩልም በሳል አመራር ሰጥተዋል።

በተለያዩ አካባቢዎች እርቅ እንዲመጣ ከጠቅላይ ዐቃቤ ሕግና የሰላም ሚኒስቴር ጋር በመሆን ውጤታማ ስራዎችን ህወታቸው እስካለፈበት ቅጽበት ድረስ አከናውነዋል።

የዓለም ሎሬት ዶክተር ጥበበ የማነብርሃን በጤናው ዘርፍ ከኢትዮጵያ አልፎ በምስራቅ አፍሪካ ሁሌም የሚዘከር አገልግሎት ሰጥተዋል።

በአለርት የህክምና ማዕከል የሥጋ ደዌ ህክምና በመስጠት የነበራቸውን አስተዋጽኦ የላቀ ሲሆን፤ በላየንስ ክለብ 40 ዓመታት ያህል አገልግለዋል።

በዚህም በትራኮማና በሌሎችም የህብረተሰብ ጤና ዘርፎች ትልቅ አስተዋጽ ነበራቸው።

የዓለም ሎሬት ጥበበ በሽግግሩ ወቅት 80 ሺህ ወታደሮች ከሱዳን እንዲመለሱ በማድረግ ሂደት የጎላ አስተዋጽኦ እንደነበራቸው ይታወሳል።

በስካውት ማህበርም በርካታ ወጣቶች አገር ወዳድ እንዲሆኑ ሰፊ ትምህርት የሰጡ ነበሩ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም