አባቶች በአንድነት ሆነው በአድዋ የተጎናጸፉት ድል በህዳሴው ግድብም ላይ መድገም እንደሚገባ የነገሌ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ

53

ነገሌ፤ የካቲት 16/2013(ኢዜአ) ጀግኖች አባቶች በአንድነት ተባብረው የውጭ ወራሪን አሳፍሮ በመመለስ በአድዋ የተጎናጸፉትን ድል በህዳሴው ግድብ ግንባታ ላይ መድገም እንደሚገባ የነገሌ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

ከነዋሪዎች መካከል የታሪክ መምህር መኮንን ይልማ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት የአድዋን ታሪካዊ ድል በታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ በአንድነት መንፈስ በመረባረብ ልንደግመው ይገባል ብለዋል፡፡

በጀግኖች አባቶች ደምና ህይወት መስዋዕትነት በአድዋ የተገኘው ድል በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የጥቁር አፍሪካዊያን ህዝቦች ነጻነት  የተረጋገጠበት እንደሆነም አስታውሰዋል፡፡

ድሉን እኛን ብቻ ሳይሆን ጥቁር አፍሪካዊያን ወንድሞቻችን ጭምር የኮሩበት በመሆኑ በየዓመቱ በክብር እያሰቡት ይገኛሉ ብለዋል፡፡

በሰላም ጊዜ መቻቻልና መከባበር በክፉ ቀን መረዳዳት መተባበርና ጀግንነት የኢትዮጵያዊያን ልዩ መገለጫዎችና ባህላዊ እሴቶች እንደሆኑም አውስተዋል፡፡

በራስ አቅም ለጀመርነው የህዳሴ ግድብ ሁለንተናዊ ድጋፍ በማድረግ አባቶቻችን በአድዋ የሰሩትን ታሪካዊ ድል መድገም ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

የቋንቋና ስነ ጽሁፍ መምህር ሙህዲን ኡስማን  በበኩላቸው የአድዋ ድል  የማይታመንና የማይቻል የሚመስል ግን የሆነ ጥቁር ህዝቦች የኮሩበትና አንገታቸውን ቀና ያደረጉበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አባቶቻችን በዘመናዊ የጦር መሳሪያ የታገዘውን ወራሪ ድል የነሱት በሰንደቅ ዓላማና በሀገር ፍቅር የጎለበተ ውስጣዊ አንድነትና ህብረት ስለነበራቸው እንደሆነ አስታውሰዋል፡፡

ወጣቱ ከብሄርተኝነት ከጎሰኝነት ፣ቂምና ጥላቻ እራሱን አርቆ በመረዳዳትና በአብሮነት በሀገሩ ሰላም ልማትና እድገት ላይ በተለይ በህዳሴ ግድብ ላይ እንዲያተኩር አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

እድሜያቸው 77 እንደሆነ የተናገሩት ሌላው የከተማዋ ነዋሪ  አቶ የሺጥላ አቦዬ በጋራ ሰርተን ሀገር መገንባትና ማሸነፍ እንደምንችል አባቶቻችን በአድዋ ያገኙት ድል የሚያስተምር ነው ብለዋል፡፡

አለመግባባቶችን በውይይትና ድርድር በመፍታት ሀገር ለማፍረስ የሚሰሩ የውስጥና የውጭ ጠላቶችን አንድ ሆኖ መታገል የህልውና ጉዳይ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ግብጽና ሱዳን የህዳሴውን ግድብ ግንባታ ለማደናቀፍ ጫና የፈጠሩት የውስጥ የፖለቲካ ልዩነቶችን እንደመልካም አጋጣሚ ለመጠቀም የተደረገ ሙከራ በመሆኑ ዜጎች ነቅተው መመከት እንዳለባቸው መክረዋል፡፡

ባለፉት 27 ዓመታት  ከአንድነት ይልቅ ልዩነቶችን ለማስፋት ሲሰራ መቆየቱንና ይህም ለጉዳት መዳረጉን አውስተው ፤ የህዳሴውን ግድብ ተባብረን ከዳር በማድረስ ያለፈውን መጥፎ ገጽታ መቀየርና ግንባታውን በመፈጸም የአድዋን አኩሪ ድል መድገም   አለብን ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም