የኢንጅነር ስመኘው በቀለ መልካም ስራ ከዳር እንዲደርስ ሁላችንም እንሰራለን-የውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር

67
አዲስ አበባ ሀምሌ 19/2010 የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ማናጀር ኢንጅነር ስመኘው በቀለ በሞት ቢለይም "መልካም ስራው ከዳር እንዲደርስ ሁላችንም እንሰራለን'' ሲሉ የውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ ጌታሁን ገለፁ፡፡ ሚኒስትሩ የኢንጅነር ስመኘውን ህልፈተ ህይወት አስመልክተው በሰጡት መግለጫ በክስተቱ ጥልቅ ሀዘን እንደተሰማቸው በመግለጽ በአደጋው ምክንያት የግድቡ ግንባታ ላይ እክል እንደማይፈጠር ተናግረዋል። የግድቡ የሲቪል ግንባታ በጥሩ ሁኔታ ላይ ያለ ቢሆንም በኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራው ላይ የታየውን መጓተት ግን ከባለድርሻ አካላት ጋር በመወያየት ችግሩን ለመፍታት እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል። ፕሮጀክቱ በፍጥነት እንዳይሄድ የያዙትን ማነቆዎች በመፈታት ላይ እንዳሉና ከቴክኒካል ጉዳዮች ውጭ ሃይድሮ ፖለቲካው በሶስትዮሽ ውይይቱ እንደተስተካከለ ተናግረዋል። የገጠሙ ችግሮችንም ቢሆን እንደ ሀገር የመፍታት አቅም እንዳለ በግድቡ የሚገነቡት ኃይል አመንጪ 16 ተርባይኖች ተመርተው በስፍራው እንደደረሱ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራው ውሰብሰብ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ረዘም ያለ ጊዜ ሊወስድ እንደሚችል ጠቁመዋል። ኢንጅነር ስመኘው በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ  ቪ ኤይት ተሽከርካሪ ውስጥ በሽጉጥ ተመትተው ህይወታቸው ማለፉንና ምርመራ እያደረገ መሆኑን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም