ተፎካካሪ ፓርቲዎችና እጩዎች ለሰብአዊ መብቶች መከበር የሚያከናውኑትን ስራ በግልጽ ማሳወቅ አለባቸው - ኢሰመኮ

57

አዲስ አበባ፤ የካቲት 15/2013(ኢዜአ)   ተፎካካሪ ፓርቲዎችና እጩዎች ለሰብአዊ መብቶች መከበር የሚያከናውኑትን ስራ በምርጫ መወዳደሪያ መግለጫቸው(ማኒፌስቶ) በግልጽ ማስቀመጥ እንደሚገባቸው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን አሳሰበ።

ፓርቲዎች ለሰብአዊ መብቶች መከበር ልዩ ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው ገልጿል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ የሚሳተፉ ባለድርሻ አካላት ሊያከብሯቸውና ሊፈጽሟቸው ይገባል ያላቸውን "ባለ ስድስት ነጥብ የሰብአዊ መብቶች አጀንዳ" ዛሬ ይፋ አድርጓል።

በአጀንዳው ተፎካካሪ ፓርቲዎችና እጩዎች ምርጫውን ካሸነፉ በኋላ ሰብአዊ መብቶች ለማክበርና ለማስከበር የሚወስዷቸውን ተጨባጭ እርምጃዎች በመወዳደሪያ ጥሪ ሰነዳቸው(ሚኒፌስቶ) በግልጽ ማሳወቅ እንደሚገባቸው ኮሚሽኑ ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

በተለይም ለመብት ጥሰት ተጋላጭ የሆኑ ሴቶች፣ህጻናት፣አካል ጉዳተኞች፣ተፈናቃዮችና ስደተኞችን ሰብአዊ መብት አጠባበቅ በተመለከተ የሚወስዷቸውን እርምጃዎች ለሕዝብ ይፋ ማድረግና ቃል መግባት እንደሚኖርባቸው አመልክቷል።

በመንግስት ስልጣን ላይ የሚገኙና ሌሎች ተወዳዳሪ እጩዎች እንዲሁም ተፎካካሪ ፓርቲዎች በአጠቃላይ የምርጫ ሂደቱ ሰብአዊ መብቶችን አክብረው በሰላማዊና በሕጋዊ መንገድ ብቻ መንቀሳቀስ እንዳለባቸው ገልጿል።

ፓርቲዎች በአባላቶቻቸውና ደጋፊዎቻቸው የሚፈጸምን የሰብአዊ መብቶች ጥሰት እንደማይታገሱና በአባላቶቻቸው የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በመመርመር ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ግልጽ የሆነ የተጠያቂነት አሰራር መዘርጋት ይጠበቅባቸዋል ነው ያለው ኮሚሽኑ።

ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የሴቶችን ተሳትፎ ማሻሻል ግልጽ አመላካቾችን በማዘጋጀት ለስርዓተ ጾታ ምላሽ የሚሰጥ መሆን እንደሚገባው አመልክቷል።

በምርጫው ሂደት የተሳተፉ ፓለቲካ ፓርቲዎችና ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በኢትዮጵያ ያለውን ውስብስብ የፖለቲካና የሰብአዊ መብቶች ቀውስ በዘላቂነት ለመፍታት መስራት እንደሚጠበቅባቸው ነው ኮሚሽኑ የገለጸው።

ከሰብአዊ መብት ጋር የተያያዙ የሕግ፣አስተዳደር ፖሊሲ ጉዳዮችን በመፈተሽ ማሻሻያ ማድረግ እንደሚገባቸው አመልክቷል።

በምርጫው ሂደት የፌዴራልና የክልል መንግስታት በተለይም የጸጥታ አካላት ተግባራቸውን በገለልተኝነትና በሃላፊነት ማከናወን እንደሚገባቸውም ተጠቁሟል።

መንግስት የፖለቲካ ፓርቲዎች፣እጩዎች፣ሲቪክ ማህበራት፣መገናኛ ብዙሃንና ሌሎች የምርጫው ተዋናዮች ያለ ምንም ገደብ፣ክልከላ፣አድልዎ፣አግባብ ያልሆነ ጣልቃ ገብነት ወይም የበቀል እርምጃ በሙሉ ነጻነት እንዲንቀሳቀሱ የሚያስችል ሁኔታ መፍጠር እንደላበት ነው ኮሚሽኑ ያመለከተው።

በተጨማሪም መንግስት የምርጫ ተዋናዮቹ መረጃ የማግኘት፣የመደራጀትና ሀሳባቸውን በነጻነት እንዲገልጹ እንዲሁም እጩዎችና የፖለቲካ ፓርቲዎች የፖለቲካ ተሳትፎ መብቶቻቸው መከበራቸውን ማረጋጋጥ እንደሚገባው አስታውቋል።

በተጨማሪም ፖለቲካ ፓርቲዎች፣እጩዎችና ሌሎች የምርጫ ተዋናዮች ከግጭት ቀስቃሽ፣የጥላቻ ንግግር እንዲሁም ከኃይል እርምጃዎች መቆጠብ እንዳለባቸው ኮሚሽኑ አሳስቧል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) የሰብአዊ መብቶች ጉዳይ በአገራዊ ምርጫው አጀንዳ እንዲሆን ማድረግ እጅጉን አስፈላጊ ጉዳይ ነው ብለዋል።

የምርጫው ተዋናዮች በኮሚሽኑ የተቀመጡትን የሰብአዊ መብት አጀንዳ ነጥቦች ትኩረት በመስጠት ቃል እንዲገቡ፣በተጠየቁት ጉዳዮች ላይ የሚገቡትን ቃልኪዳን እንዲያሳውቁና በአጀንዳው በተቀመጠው መሰረት ሰብአዊ መብቶችን በማክበር እንዲቀሳቀሱ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም