የአድዋ ድል እሴቶችን ለሀገር አንድነትና ብልጽግና ማዋል ይገባል ተባለ

101

ደብረብርሃን፣ የካቲት 15/2013(ኢዜአ) ጀግኖች አባቶቻችን በአድዋ የተቀናጁትን የድል እሴት በመጠበቅ ለሃገር ግንባታና ብልጽግና ማዋል እንደሚገባ በአማራ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን አስተያታቸውን የሰጡ አባት አርበኛና ምሁር አስገነዘቡ።

የሰሜን ሸዋ ዞን አባት አርበኞች ማህበር ሊቀመንበር አቶ ተክለሥላሴ ከበደ ለኢዜአ እንደገለጹት የአደዋ ድል ለመላው ዓለም ህዝቦች እኩልነትን፤ ለችግር አይበገሬነትን ያስተማረ ታሪካዊ ክስተት ነው።

ድሉ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን የጥቁር ህዝቦች ታሪክ ቢሆንም በተገቢው መንገድ ተጠብቆ ለቱሪዝም ልማትና ለሃገር ግንባታ ያልተሰራበት ሃብት መሆኑን ተናግረዋል።

"አባቶች መስዋትነት ከፍለው ያቆዩት የጀግንነት ታሪክ በወጣቱ ዘንድ ተገቢው እውቅና እንዳይኖረው ባለፉት 27 ዓመታት የጁንታው ቡድን ህዝቡን በዘር በመከፋፈል የሃሰት ትርክት ሲረጭ ቆይቷል" ብለዋል።

ወጣቶች ከአድዋ ድል ህብረትና አንድነትን በመማር ከእርስ በእርስ ግጭት፣ ጥላቻና ከሃሰት ትርክት ወጥተው ሃገራቸውን ከድህነትና ኋላ ቀርነት አስተሳሰብ ለማላቀቅ ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

አባቶች በአድዋ ያሳዩትን አንድነት፣ የሀገር ፍቅርና  ወኔ ከመዘከር ባለፈ የድል ቦታዎችን በማልማት ታሪኩን ሰንዶ ለቱሪዝም ልማት ማዋል እንደሚገባም አመልክተዋል።

በደብረ ብርሃን ዩኒቨርስቲ የቱሪዝም ማኔጅመንት ትምህርት ክፍል ሃላፊ መምህር አስራት ደሴ በበኩላቸው ጀግኖች ኢትዮጵያውያን በአንድነት በመነሳት ለሃገራቸው ነፃነት ያበረከቱት ድል መቼም ቢሆን ሊረሳ የማይችል መሆኑን ተናግረዋል።

ድሉ ለኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳይሆን መላው ጥቁር ህዝቦች ከጭቆና ቀንበር የተፈቱበትና ነፃነታቸውን የተጎናጸፉበት መሆኑን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያዊያን ከአድዋ ድል በመማር የብሄር፣ የእምነት፣ የፖለቲካ አመለካከትና የቋንቋ ልዩነትን አቻችለን ለአንዲት ጠንካራ ሃገር ግንባታና ለሰላም መስፈን መትጋት ይጠበቅብናል" ብለዋል።

"የአድዋ የድል ታሪክ በትክክል ተሰንዶ በሁሉም አካባቢዎች ተሰራጭቶ ለቱሪዝም ሃብት ልማት በማዋል ሀገሪቱ ከዘርፉ ተጠቃሚ እንድትሆን መስራት ያስፈልጋል" ሲሉም ተናግረዋል ።

በመንግስት  በኩልም የሀገር ፍቅር ስሜት ክፍተትን ለመሙላት የአድዋ ድል ታሪክን በስርአተ ትምህርት በማካተት ህጻናት ከታች ጀምሮ ሀገራቸውን እንዲያውቁና እንዲወዱ ለማድረግ መሰራት እንዳለበት አመልክተዋል።

የሰሜን ሸዋ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ሃላፊ ወይዘሮ ትእግስት መኳንቴ በበኩላቸው 125ኛውን የአድዋ ድል በዓል በድምቀት ለማክበር እየተሰራ መሆኑን ተናግረው በዞኑ ከየካቲት 21 እስከ 23 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ ታሪካዊ ቦታዎችን በማስተዋወቅ፣ የ8 ኪሎ ሜትር ሩጫ በማካሄድና በሌሎች ስነ ስርአቶች በአሉን ለማክበር ዝግጅት መጠናቀቁን  አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም