የደቡብ ፣ ሶማሌ ክልሎችና የድሬደዋ አስተዳደር በኢንጅነር ስመኘው በቀለ ድንገተኛ ሞት የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ገለጹ

79
ሀዋሳ ጂግጂጋ ድሬዳዋ ሀዋሳ 19/2010 የደቡብ እና የሶማሌ ክልላዊ መንግስት እንዲሁም የድሬደዋ አስተዳደር ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መሪ መሃንዲስና ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ስመኘው በቀለ ድንገተኛ ሞት የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ገለጹ፡፡ የደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልላዊ መንግስት ለኢዜአ በላከው የሀዘን መግለጫ እንዳመለከተው ኢንጂነር ስመኘው በከባድ መስዋዕትነት ሃገራቸውንና ወገናቸውን በታላቅ ቆራጥነት ፣ቅንነትና ኢትዮጵያዊ እልህ ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡ ድንገት በአሳዛኝ ሁኔታ ከዚህ አለም በሞት በተለዩት ኢንጅነር ስመኘው በቀለ ህልፈት የክልሉ መንግስትና ህዝብ  የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን በመግለጽ ለቤተሰቦቻቸውና ለመላው ኢትዮጵያዊያን መጽናናትን ተመኝቷል፡፡ በተመሳሳይ የሶማሌ  ክልላዊ መንግስት በላከው የሀዘን መግለጫ በታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ  ግንባታ ሂደት  የላቀ አሻራ ያላቸው ኢንጀነር ስመኘው በቀለ ድንገተኛ ሞት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን በመግለጽ ለቤተሰቦቻቸውና ለመላው ኢትዮጵያ ህዝብ መጽናናትን ተመኝተዋል፡፡ የኢንጂነሩ ህይወት ቢያልፍም የጀመሩትን ፕሮጀክት ከዳር ለማድረስ የክልሉ መንግስትና ህዝብ  የሚያደርጉት ተሳትፎና ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በመግለጫው አረጋግጠዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሶማሌ ህዝብ ዴሞክራሳዊ ፓርቲ (ኢሶህዴፓ) እንዲሁ የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ገልጿል፡፡ በሌላ በኩል የድሬዳዋ አስተዳደርና ህዝብ  በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ስመኘው በቀለ ድንገተኛ ሞት  የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን በመግለጽ በእሳቸው ግንባር ቀደም መሪነት የተጀመረው ፕሮጀክት ዳር ለማድረስ ድጋፉቸውን አጠናክረው  እንደሚቀጥሉም አስታውቀዋል፡፡ ለቤተሰቦቻቸው መፅናናትን ተመኝተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም