ኢትዮጵያዊያን በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የእጅ አዙር የቅኝ ግዛት አስተሳሰብን ቀይረዋል -ምሁራን

79

አዲስ አበባ፣ የካቲት 13/2013 ( ኢዜአ)  ኢትዮጵያዊያን ዳግማዊ የአድዋ ድልን በታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ግንባታ በሚያደርጉት ተሳትፎ የእጅ አዙር የቅኝ ግዛት አስተሳሰብን መቀየራቸውን ምሁራን አመለከቱ።

ግድቡ አፍሪካዊያን በራሳቸው አቅም ማደግና መልማት እንደሚችሉ ማሳያ ነው ብለዋል።

አውሮፓዊያን የአፍሪካን የተፈጥሮ ሀብትና የሰው ጉልበት ለመቀራመት ተስማምተው የቅኝ ግዛት ውላቸውን በኃይል መተግበር ሲጀምሩ ኢጣልያም አፈሙዟን ወደ ኢትዮጵያ ወድራ ነበር።

በኢትዮጵያና በኢጣልያ መካከል ለተደረገው የአድዋ ጦርነት መነሻ ከሆኑት ምክንያቶች አንዱ በእንግሊዝ ፈቃድና በኢጣልያ ተግባሪነት የዓባይ ወንዝንና ሌሎች የኢትዮጵያ ተፋሰሶችን የመያዝ ፍላጎት መሆኑን የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የታሪክና የሕግ ምሁሩ ዶክተር አልማው ክፍሌ ይናገራሉ።

የአውሮፓዊያኑን ተንኮልና የወረራ ግብ የተረዱ ኢትዮጵያዊያን መሪዎችና ሕዝቡ አስተባብረው የአገራቸውን ሀብት ከዘረፋ ለመታደግና የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ለማስከበር ወደ አድዋ ተመሙ።

በድንቅ የጦር ስትራቴጂ በመሪዎች የማስተባበር ችሎታና በኢትዮጵያዊያን የተባበረ ክንድ ኢጣልያን ''አይቀጡ ቅጣት'' ቀጥተው በማሸነፍ የአውሮፓን የቅኝ ገዛት መንፈስ ሰበሩ።

ኢትዮጵያዊያን የተቀዳጁት ድል በመላው ዓለም የጥቁሮች ነፃነትንና የአፍሪካን የፀረ ቅኝ አገዛዝ ንቅናቄ ወልዷል።

የዓባይ ወንዝን በኃይል በመጠቀም ኢትዮጵያ ውስጥ ማምረትና መዝረፍ አይቻልም በሚል ተጋድሎ የተገኘው የአድዋ ድል፤ የተፈጥሮ ሃብታችንን በራሳችን አቅም መጠቀም እንችላለን የሚል ዕሳቤን በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብግ ግንባታ እውን ማድረግ አስችሏል።

ኢትዮጵያ እነ ግብፅ ወደ ቅኝ ገዥዎቻቸው የወሰዱትን የዓባይ ወንዝ ጉዳይ ወደ አፍሪካ በመመለስ የአፍሪካን ችግሮች በአፍሪካዊያን መፍታት ይቻላል የሚል ሌላ ድል መቀዳጀቷን ያብራሩት በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የዲፕሎማሲና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህሩ እንዳለ ንጉሴ ናቸው።

ኢትዮጵያዊያን በግድቡ ላይ የመጀመሪያውን ዙር የውሃ ሙሌት በማካሄድ ዳግማዊ አድዋን በተግባር ማሳየት ችለዋል ብለዋል።

በኢኮኖሚም በነጻነትም ፖሊሲዎችን መንደፍ መተግበር ማስፈፀም ይቻላል።

ዶክተር አልማው እንደሚሉት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሲጀመር ኢትዮጵያዊያን እውቀት አቅምና ገንዘብ ስለሌላቸው ''አይገነቡትም'' የሚል አቋም በውጭ ዜጎች ዘንድ ነበር።

ሆኖም የግድቡ ግንባታ በኢትዮጵያዊያን አቅምና እውቀት መጀመሩ የግብፅን የተሳሳተ የፖሊሲ አካሄድ ከማስቀየር አልፎ፣ የውጭ ዜጎች የሕግና የፍትሕ ልኬት ባለቤት ነው የሚሉትን የቅኝ ግዛት ሥነ ልቡና ሰብሯል።

ሕዝቡ የግድቡን ግንባታ ለማጠናቀቅ አንድነቱን በማጠናከር የገንዘብ፣ የእውቀትና የጉልበት አስተዋፅኦውን እንዲቀጥልም ምሁራኑ የአደራ ምክራቸውን ለግሰዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አጠቃላይ የግንባታ ደረጃ በአሁኑ ወቅት ከ78 በመቶ በላይ ደርሷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም