በህገ ወጥ መንገድ ተከማችቶ የተገኘ 5 ሺህ 626 ኩንታል ስኳርና ጨው በቁጥጥር ስር ዋለ

146

ደሴ ፣የካቲት 13/2013 (ኢዜአ) በደቡብ ወሎ ዞን ቃሉ ወረዳ በህገ ወጥ መንገድ ተከማችቶ የተገኘ 5 ሺህ 626 ኩንታል ስኳርና አዮዲን የሌለው ጨው በቁጥጥር ስር መዋሉን የወረዳው ንግድና ገበያ ልማት ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ሰይድ ይማም ለኢዜአ እንደገለጹት ፤  ስኳር እና ጨዉ የተገኘው ትናንት ከህብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ ነው።

በጥቆማው መሰረት ከፖሊስ ጋር በመቀናጀት ባደረጉት ክትትል አራት ሺህ 26 ኩንታል ስኳር እና አንድ ሺህ 600 ኩንታል አዮዲን የሌለው   ጨው በህገ ወጥ መንገድ በተለያዩ መጋዘኖች ተከማችቶ ማግኘታቸውን አስታውቀዋል።

በጉዳዩ የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ለማዋል የጸጥታ ኃይሉ እየሰራ ነው ብለዋል፡፡

አካባቢው ገጠር በመሆኑ የጸጥታ ኃይል ሊያየው አይችልም በሚል የተከማቸ መሆኑን ጠቁመው፤  ህብረተሰቡ ላደረገው ትብብር ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ህገ ወጥነትን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም