ሴቶች በሀገር ግንባታ ሂደት ጉልህ ሚና እንዲጫወቱ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል--ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ

159

ሀዋሳ፣ የካቲት 13/2013 (ኢዜአ) ሴቶች በሀገር ግንባታ ሂደት ጉልህ ሚና እንዲጫወቱ ለማስቻል በመንግስት የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ገለጹ፡፡

ሚኒስቴሯ ከደቡብ ክልል ሴክተር መሥሪያ ቤት ሴት የመንግስት ሠራተኞች ጋር ለውጡ ለሴቶች ያመጣው ትሩፋትና በቀጣይ ሂደት ዙሪያ በመከሩበት ወቅት እንዳሉት የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ የወጡ የህግ ማዕቀፎች ባለፉት 28 ዓመታት ከንግግር ባለፈ በተግባር እየተተረጎሙ አልነበረም።

የለውጡ መንግስት በፌዴራል ደረጃ ከፍተኛ አመራር ቦታ ላይ 50 በመቶ ሴቶችን ማድረጉ ለመላው አፍሪካና ሌሎች የአለም ሃገራት ምሳሌ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ይህም የለውጡ ማህበራዊ መሠረት ጠንካራ እንዲሆን ማስቻሉን ያነሱት ሚኒስትሯ ይህንን እስከታችኛው ለማውረድ በትኩረት መሰራት እንዳለበት የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል።

እነዚህ ጉዳዮች የቀጣይ ትኩረት አቅጣጫዎች መሆናቸውን ጠቁመው አዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ የሴቶች ብቁነትና ተወዳዳሪነት ለማጎልበት ልዩ ትኩረት መሰጠቱን አስረድተዋል፡፡

የሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ስኬቶች እየሰረጹ እንዲሄዱና ተጽዕኖ ፈጣሪነታቸው እንዲጨምር በአስተሳሰብ ልቆ መገኘት እንደሚገባም ተናግረዋል።

ጠንካራ አደረጃጀት በመፍጠር መታገል፣ መወያየት፣ መደማመጥ፣ መደጋገፍና ራስን ማብቃት ከሴቶች እንደሚጠበቅ አስታውቀዋል።

ለሴቶች ተጠቃሚነት የተመቸ፣ ጠንካራና የመንግስት ግንባታ ዕውን እንዲሆን በስድስተኛው ሃገራዊ ምርጫ በንቃት እንዲሳተፉና ሠላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የደቡብ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ወይዜሮ ነኢማ ሙኒር በበኩላቸው ከለውጡ ወዲህ ለሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት የተሰጠው ትኩረት መልካም መሆኑን ገልጸዋል።

ይህም በተጠናከረ መልኩ እስከታች ድረስ እንዲወርድ የምክክር መድረኮች በመፍጠር አዋጆችና ደንቦች ተፈጻሚ እንዲሆኑ እየተሠራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

ከምክክር መድረኩ ተሳታፊዎች መካከል ወይዘሮ ወርቅነሽ ጎኣ በሰጡት አስተያየት ከለውጡ ወዲህ በሃገሪቱ እየተመዘገበ ላለው ዘርፈ ብዙ ዕድገት የሴቶች ተሳትፎ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል።

መንግስት የሥርዓተ ጾታ ጉዳይ ላይ በማተኮር አዋጆችና ደንቦች በአግባቡ መተግበራቸውን መከታተል እንዳለበት ጠቁመዋል።

ሌላው ተሳታፊ ወይዘሮ ፋናዬ ሙሉነህ በበኩላቸው ሀገራዊ የለውጥና ብልጽግና ጉዞ እንዲሳካ ከመንግስት ጎን በመቆም የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።

"የሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለሁለንተናዊ ብልጽግና" በሚል መሪ ሀሳብ የተካሄደው የምክክር መድረክ በክልሉ በሚገኙ ሁሉም መዋቅሮች እንደሚቀጥል ተመልክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም