አገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች በብሔራዊ መግባባት ላይ የጀመሩት ድርድር ተራዘመ

127
አዲስ አበባ  ሀምሌ 19/2010 የአገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከገዢው ፓርቲ ጋር በብሔራዊ መግባባት ላይ የጀመሩት ድርድር ላልተወሰነ ጊዜ እንዲራዘም ተስማሙ። ኢዴፓ፣ ቅንጅት፣ አንድነት፣ መኢብን፣ መኢአድ፣ ኢዴህ፣ ኢዴአን፣ ኢሠዴፓና አትፓን ጨምሮ የተለያዩ 15 አገር አቀፍ ፓርቲዎች ላለፈው አንድ ዓመት ከመንፈቅ ለሆነ ጊዜ ከኢህአዴግ ጋር ድርድር ሲያካሄዱ ቆይተዋል። ፓርቲዎቹ ይህንኑ ሂደት በመቀጠል በብሔራዊ መግባባት ጉዳይ ዙሪያ ለመደራደር በዛሬው ዕለት ተገናኝተው የነበረ ቢሆንም በርእሰ ጉዳዩ ላይ የሚካሄደው ውይይት ሁሉን አቀፍ ማድረግ ይችል ዘንድ እንዲራዘም የኢህአዴግ ተወካዮች ጠይቀዋል። በድርድሩ ሂደት እስካሁን ያልተሳተፉ በአገር ውስጥ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆኑ በአሁኑ ወቅት መንግስት ባደረገው ጥሪ ከውጭ ወደአገር የገቡ የፖለቲካ ማህበራት የድርድሩ አካል ቢሆኑ ሂደቱ ውጤታማ ይሆናል የሚል ሀሳብም ከኢህአዴግ ተወካዮች ቀርቧል። ከዚህ በተጨማሪ ገዢው ፓርቲና የሚመራው መንግስት በአሁኑ ወቅት የለውጥ ተግባራትን እያካሄደ በመሆኑ በርካታ ችግሮች ይቀረፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም አብራርተዋል። በብሔራዊ መግባባት የተጀመረው ድርድር ሁሉን አቀፍ እንዲሆን ገለልተኛ ኮሚቴ ተቋቁሞ ጥናትን ጨምሮ ምቹ ሁኔታዎችን የመፍጠር ተግባር በመከናወን ላይ መሆኑንም አስረድተዋል። በመሆኑም በኮሚቴው ተጠንቶ በሚቀርበው ውጤት መሰረት ሁሉም አካላት የተሳተፉበት ድርድር ለማካሄድ እንዲቻል በብሔራዊ መግባባት ርእሰ ጉዳይ ላይ የተጀመረው ደርድር እንዲራዘም ኢህአዴግ ጠይቋል። ይህን ተከትሎ አቋማቸውን ያንፀባረቁት ሁሉም ተደራዳሪ ፓርቲዎች የድርድር ሂደቱ ሁሉን አቀፍ እንዲሆን የሚሹ መሆናቸውን በመግለፅ ገዢው ፓርቲ ባቀረበው 'የይራዘም' ሀሳብ ላይ ከስምምነት ደርሰዋል። በዚህ መሰረት ገዢው ፓርቲ ሁሉን አቀፍ ድርድር ለማካሄድ የሚያስችሉ ሁኔታዎችን አመቻችቶ እስኪያሳውቅ ድረስ ድርድሩ ላልተወሰነ ጊዜ ተራዝሟል። በሌላ በኩል የድርድሩ ተሳታፊ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአሁኑ ወቅት ያለው የአገሪቱ የፀጥታ ችግር አስጊ በመሆኑ ውይይት ማድረግ አለብን የሚል ጥያቄ አቅርበዋል። ገዢው ፓርቲም በአገራዊ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ከሁሉም ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ለመወያየት መድረክ እንደሚያዘጋጅ አስታወቋል። ከዚህ ቀደም ደርድሩን አቋርጦ ወጥቶ የነበረው የመላው አማራ ድርጅት ፓርቲ ደግሞ ለመመለስ ያቀረበው ጥያቄ ይሁንታ በማግኘቱ በዛሬው ድርድር ተሳትፏል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም