ኢንስቲትዩቱ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ያሰለጠናቸውን ከአንድ ሺህ በላይ ሰልጣኞች አስመረቀ

89

አዲስ አበባ፣ የካቲት 13/2013 ( ኢዜአ) የኢትዮጵያ ቴክኒክ፣ ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኢንስቲትዩት በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ያሰለጠናቸውን ከአንድ ሺህ 900 በላይ ሰልጣኞችአስመረቀ።

ኢንስቲትዩቱ ወደ ቴክኒክ ዩኒቨርሲቲነት ማደጉም በዚሁ ወቅት ተገልጿል።

ኢንስቲትዩቱ ለስድስተኛ ጊዜ ዛሬ ያስመረቃቸው ተማሪዎች ከሰለጠኑበት የትምህርት መስኮች መካከል ማኑፋክቸሪንግ ፣ የማዕድን፣ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና የቆዳ ስራ ይገኙበታል። 

ከተመራቂዎቹ መካከል 1ሺህ 574ቱ በመጀመሪያ ዲግሪ፤ 346ቱ ደግሞ በሁለተኛ ዲግሪ መርሃ ግብር ትምህርታቸውንየተከታተሉ ናቸው።

በዛሬው ዕለት በሁለቱም መርሃ ግብሮች ከተመረቁት ተማሪዎች መካከል 243 የሚሆኑት ሴቶች ናቸው።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተሻለ በሬቻ፤ ምሩቃኑ በሰለጠኑበት የሙያ መስክ አገራቸውንና ህዝባቸውን በቅንነት በማገልገል ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

በአሁኑ ወቅት ኢንስቲትዩቱ በቴክኒክና ሙያ ስልጠና ዘርፍ የሚታየውን የመምህራን እጥረት ለማቃለል በስድስት ክልሎች ካሉ የፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች ውስጥ 15 ሳተላይት ማዕከላትን በመክፈት ስልጠና እየሰጠ ነው ብለዋል።

በተጨማሪም የስልጠና ፕሮግራሞቹን በማስፋት በሰባት ፋክሊቲዎች 33 የቅድመ ምረቃና የድሕረ ምረቃ ፕሮግራሞች በማደራጀ ስልጠናዎች መስጠት መጀመሩን ገልጸዋል።


የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ሳሙዔል ኡርቃቶ ፤ ኢንስቲትዩቱ ወደ ቴክኒካል ዩኒቨርሲቲ ማደጉን አብስረዋል። 

ይሕም ተቋሙ ተልዕኮውን በአግባቡ እንዲወጣ ያስችለዋል ነው ያሉት።

ከተመራቂ ተማሪዎች መካከል በከፍተኛ ማዕረግ ተሸላሚ የሆነችው ተማሪ ራሔል ተከሰተ፤ ሁሉም በተሰማራበት ውጤታማ በመሆን አገሩንና ራሱን የሚጠቅም ዜጋ ሊሆን ይገባል ብላለች።

በየትኛውም መስክ የተለያዩ ችግሮች የሚገጥሙ ቢሆንም ይሔን ተቋቁሞ በውጤት መብቃት ግን ከፍተኛ ደስታን ያጎናጽፋል ነው ያለችው።

ኢንስቲትዩቱ በ1997 ዓ.ም ነበር በአዲስ አበባ ቴክኒክ እና ሙያ ትምህርት እና ሥልጠና ኤጀንሲ ሥር የኢትዮ-ቻይና ፖሊ ቴክኒክ ሆኖ የተቋቋመ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም