አምባሳደሮቹ የኢትዮጵያን ገጽታ በመገንባት አገራቸው የምትፈልገውን የዲፕሎማሲ ስራዎች እንዲፈፅሙ ተጠየቀ

70

አዲስ አበባ፣ የካቲት 13/2013 ( ኢዜአ) በተለያዩ አገራት ኢትዮጵያን የወከሉ አምባሳደሮች የአገር ገጽታን በመገንባትና ብሔራዊ ጥቅምን በማስከበር አገራቸው የምትፈልገውን የዲፕሎማሲ ሥራዎች እንዲፈጽሙ ተጠየቀ።

በተለያዩ አገራት ለተሾሙ አዳዲስ አምባሳደሮችና ምክትል ሚሲዮን መሪዎች በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለሁለት ሳምንታት ሲሰጥ የነበረው ስልጠና ትናንት ተጠናቋል። 

በጥር 2013 ዓ.ም ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በአፍሪካ፣ በኤስያ፣ በአውሮፓና መካከለኛው ምስራቅ አገራት ኢትዮጵያን ለሚወክሉ አምባሳደሮች ሹመት መስጠታቸው ይታወሳል።

በዚህም መሰረት ስምንት አምባሳደሮች እና አምስት ምክትል ሚሲዮን መሪዎች አቅማቸውን ለመገንባት በሚያስችሉ 14 ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ስልጠናዎች ሲሰጣቸው ቆይቷል።

ስልጠና ካገኙባቸው ርዕሰ ጉዳዮች መካከል የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ፣ የጎረቤት አገራትና የድንበር ዲፕሎማሲ እንዲሁም የውሃ፣ ኢኮኖሚና የዲያስፖራ ዲፕሎማሲ ይገኙበታል።

በተጨማሪም በሁለትዮሽና በዓለም አቀፍ ተቋማት ግንኙነቶች፣ በፐብሊክ ዲፕሎማሲ እና በሚኒስቴሩ የ10 ዓመት ዕቅድ ላይ ስልጠና ተሰጥቷቸዋል።

በስልጠናው መዝጊያ ላይ ንግግር ያደረጉት በሚኒስቴሩ የሰው ሀብት ልማት ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ረጋሳ ከፋለ ኢትዮጵያ ቀደምት የዲፕሎማሲ ታሪክና ልምድ ያላትና በበርካታ አገራት ሚሲዮን ያላት አገር መሆኗን አንስተዋል።


አምባሳደሮች በዲፕሎማሲው መስክ ዓለም ከደረሰበት ደረጃ በመድረስ ከስልጠናው ያገኟቸውን ግብዓቶች በመጠቀም የኢትዮጵያን ገጽታ በመገንባትና ብሔራዊ ጥቅሟን በማስከበር ተልዕኳቸውን በስኬት እንዲፈጽሙ ጠይቀዋል።

በዚህም በዜጋ፣ በኢኮኖሚና በውሃ ዲፕሎማሲ በተለይም ስለ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ በማስረዳት የኢትዮጵያን ጥቅም የማስከበር ዲፕሎማሲያዊ ሥራዎችን ማከናወን እንደሚጠበቅባቸው አስረድተዋል።

በተመሳሳይ መንግስት በሰሜን ኢትዮጵያ ያካሄደውን ሕግ የማስከበር ዘመቻ ተከትሎ የኢትዮጵያን ስም የሚያጠለሹ የተለያዩ አፍራሽ እንቅስቃሴዎች እየተካሄዱ መሆኑን ገልጸዋል።

አዳዲስ ሹመኛ አምባሳደሮች በተመደቡባቸው አገራት እውነታውን የማሳወቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

ስልጠናው ከተሰጣቸው አምባሳደሮችም አምባሳደር ሀደራ አድማሱ-በጋና፣ አምባሳደር ነቢል ማሀዲ-በደቡብ ሱዳን፣ አምባሳደር መላኩ ለገሰ- በሴኔጋል፣ አምባሳደር አደም መሐመድ-በቱርክ፣ አምባሳደር ወይንሸት ታደሰ- በኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ፣ አምባሳደር ደሚቱ ሐምቢሳ-በኢጣልያ፣ አምባሳደር ሙክታር ከድር-በአውስትራሊያ እና አምባሳደር ሌንጮ ባቲ-በሳዑዲ ዓረቢያ እንዲሰሩ ተመድበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም