‘‘መከላከያ የባንክ ሂሳቡን ወደ ኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክ አዘዋወረ'' ተብሎ የተሰራጨው መረጃ ከእውነት የራቀ ነው- የአገር መከላከያ ሰራዊት

130

አዲስ አበባ፣ የካቲት 13/2013 ( ኢዜአ) አንዳንድ የግልና የማህበራዊ ሚዲያዎች ‘‘መከላከያ የባንክ ሂሳቡን ወደ ኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክ አዘዋወረ'' በሚል ያሰራጩት ዘገባ ፍፁም የተሳሳተና እውነታነት የሌለው ነው ሲል የአገር መከላከያ ሰራዊት ገለፀ።

የመከላከያ ኢንዶክትሪኔሽን ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል መሐመድ ተሰማ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለኢዜአ በሰጡት መግለጫ ዋዜማ ሬዲዮ ‘‘ የተወሰኑ የመከላከያ ተቋማት የባንክ ሂሳባቸውን ወደ ኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክ አዙረዋል “ብሎ ያወጣው ዘገባ የተሳሳተ ነው ብለዋል።

ዋዜማ ሬዲዮ የዘገበውን በዋቢነት በመጠቀም ኢትዮ ፎረም እና አዲስ ሞኒተር የተባሉ ሚዲያዎችም ይህንኑ የሀሰት መረጃ ማሰራጨታቸውን ጠቁመዋል።

ይሁን እና የአገር መከላከያ ተቋም የፌዴራል ተቋም በመሆኑ የመንግስት ባንክ በሆነው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብቻ እንደሚጠቀም አረጋግጠዋል።

እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ የተሳሳተ መልዕክት ያስተላለፉት እነዚህ ሚዲያዎች ዓላማቸው ከእውነት የራቁና ወጣ ያሉ ህዝብን ብዥታ ውስጥ የሚከቱ መልዕክቶችን በማስተላለፍ እውቅናና ገቢ ለማግኘት እየተንቀሳቀሱ ነው ብለዋል።

እነዚህ አካላት ተቋሙን በግልጽ ከመወንጀል ባሻገር ያስተላለፉት መልዕክትም ከፋፋይ እና በህዝቡና በሰራዊቱ መካከል ጥርጣሬን የሚፈጥር የህግ ጥሰት ያለበት ዘገባ ነው ብለዋል ሜጄር ጄኔራል መሐመድ።

መከላከያ በየጊዜው መሰል የስም ማጥፋት ዘገባዎች እየወጡ በዝምታ እያለፋቸው እና አንዳንዶቹንም እንዲያስተካክሉ ሲያደርግ መቆየቱን ሜጀር ጄኔራል መሐመድ ገልፀዋል፡፡ 

በአሁኑ ወቅት ከህግ ማስከበር ዘመቻው ጋር ተያይዞ ሰራዊቱ የህይወት መስዋትነት ጭምር እየከፈለ ባለበት ሁኔታ እንደዚህ አይነት የስም ማጥፋት በሰራዊቱ ላይ ሲደርስ አሳዛኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሰራዊቱ ለአገር ሉዓላዊነት ከፍተኛ መስዋትነት ከፍሎ አገር እያስቀጠለ ባላበት ጊዜ እንደዚህ አይነት ወሬ የሚነዙ አካላት ዓላማ ጁንታው እያራመደ ያለውን የዘረኝነት ቅስቀሳ ማስፈፀም ነው ብለዋል ሜጄር ጄኔራል መሐመድ።

የመከላከያ ተቋምም ሆነ በስሩ ያሉ ድርጅቶች የቀየሩት አካውንትም ሆነ የተዘዋወረ ገንዘብ አለመኖሩን ህዝቡ ሊገነዘብ ይገባል ነው ያሉት።

ይህን የስም ማጥፋት ዘመቻ በዝምታ የማለፉ ጉዳይ ማብቃቱን የገለፁት ሜጄር ጄኔራሉ ይህን ድርጊት የፈፀሙ የሚዲያ አካላት የመከላከያ ሰራዊት በአገሪቱ ህግ መሰረት ተጠያቂ እንደሚያደርግ ነው ያረጋገጡት።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሜጀር ጄኔራል መሐመድ ተሰማ ጁንታው በዋሻ ውስጥ ሆኖ የትግራይን ህዝብ ለማደናገር የሚያደርገው ጥረት አይሳካም ሲሉ ተናግረዋል።

አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ህወሓት የተባለ ድርጅት መሬት ላይ የለም በማለት ነው የገለጹት።

"ጁንታው መቃብር ፈንቅሎ ሊወጣ አይችልም፤ ራሱ በለኮሰው እሳት ተለብልቦ ጠፍቷል" ብለዋል።

ይሁን እንጂ ተበታትነውና በዋሻ ውስጥ ተደብቀው የሚገኙ የጁንታው ትርፍራፊዎችና ከፍተኛ ተከፋይ አክቲቪስቶቻቸው አሁንም የሐሰት ወሬ እየነዙ ይገኛሉ ነው ያሉት።

የጁንታው ቃል አቀባይ የነበረው ጌታቸው ረዳ ከሰሞኑ በስልክ አስተላለፈው ተብሎ የወጣው መልዕክት  የትግራይ ወጣቶችን ለማደናገር የተደረገ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

በመጨረሻም የቀሩትን የጁንታ ቡድን አባላት ከተደበቁበት ጉድጓድ ለማውጣት የአገር መከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ ርብርብ እያደረገ ነው ያሉት ሜጀር ጄኔራል መሐመድ ተሰማ ጁንታውን የማደንና ሰላም የማስከበሩ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም