የሕብረተሰቡ የልማት ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ አጋርነታችንን እናጠናክራለን.... በአዳማ ባለሀብቶች

54
አዳማ ሀምሌ 19/2010 ህዝቡ የሚያነሳቸው የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ አጋርነታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ በአዳማ ከተማ አስተያየታቸውን የሰጡ ባለሀብቶች ገለፁ። መንግስት የጀመረውን ሁሉን አቀፍ ለውጥ ከዳር ለማድረስ በገንዘባቸውና በእውቀታቸው እንደሚያግዙም ባለሀብቶቹ ተናግረዋል ። ከከተማዋ ባለሃብቶች መካከል አቶ አንዋር ሰይድ እንዳሉት በአዳማ ከተማ እየጨመረ የመጣውን የህዝብ የመልማትና የማደግ ፍላጎት ለማሟላት በመንግስት አቅም ብቻ የሚቻል ባለመሆኑ የባለሀብቱን እገዛ ይፈልጋል ። ባለሀብቱ በኢንቨስትመንት መስኮች የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎችን በገንዘብና በእውቀት መደገፍ እንደሚገባው ተናግረዋል ። በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በመስተዳደሩ የተከናወኑ  የልማት ሥራዎችን ባላቸው የምህንድስና ሙያ ከማገዝ በተጨማሪ ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ በጥሬ ገንዘብ ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጽዋል። "የአዳማ ከተማ ልማትና እድገት ከኛ ጋር የተቆራኘ ነው" ያሉት ደግሞ በኮንስትራክሽ ዘርፍ የተሰማሩት ኢንጂነር ድሪባ ደፈርሳ ናቸው። ለእዚህም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለመሰረተ ልማት ሥራዎች ማሽነሪዎችን ከማቅረብ ጎን ለጎን ከ7 ሚሊዮን ብር በላይ በጥሬ ገንዘብ ድጋፍ ማድረጋቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል። ከሶማሌ ክልል የተፈናቀሉ የክልሉ ተወላጆችን መልሶ ለማቋቋም እየተደረገ ያለውን ጥረት ለማጋዝ በአዳማ ከተማ 80 መኖሪያ ቤት በመስራት ለመስተዳደሩ ማስረከባቸውንም ጨምረው ገልፀዋል። በከተማዋ በሚከናወነው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማቶች በንቃት በመሳተፍ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከመንግስት ጋር በቅንጅት የጀመሩትን ሥራ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ኢንጂነር ድሪባ አስታውቀዋል። የአዳማ ቆርቆሮ ፋብሪካ ባለቤት አቶ አብዱልሃኪም ሁሴን በበኩላቸው በተጠናቀቀው የ2010 በጀት ዓመት ለተለያዩ መሰረተ ልማቶች ግንባታ ከ11 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድርጋቸውን ገልጸዋል። በከተማው የቦኩ ሸነን ክፍለ ከተማ የአስተዳደር ህንጻዎችን በራሳቸው ሙሉ ወጪ ገንብቶ ለማስረከብ ከመስተዳደሩ ሥራውን ተረክበው በግንባታ ላይ መሆናቸውንም ተናግረዋል። የአዳማ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ መስፍን አሰፋ በበኩላቸው በ2010 በጀት ዓመት በከተማዋ ለተከናወኑ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማቶች ባለሀብቶች ከ130 ሚሊዮን ብር በላይ በጥሬ ገንዘብ ድጋፍ አድርገዋል። የከተማዋን ህብረተሰብ ከልማቱ ተጠቃሚ ለማድረግ አስተዳደሩ በሚያደርገው ጥረት የባለሃብቶች ድጋፍ አስተዋጽኦው የጎላ በመሆኑ አሁን እያሳዩት ያለውን የልማት አጋርነት አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም