በባሌ ጎባ ተፈጥሮ የነበረው ግጭት በእርቀ ሰላም ተጠናቀቀ

59
ጎባ ሀምሌ 19/2010 አሳሳቾች በፈጠሩት ችግር ሰሞኑን በባሌ ጎባ ከተማ የነበረው ግጭት እርቀ ሰላም በማውረድ ተጠናቀቀ፡፡ ከኦሮሚያ ኃይማኖት ጉባኤ የመጡት መለከገነት ቆሞስ  ገብረማሪያም ነጋሳ  በእረቀ ሰላሙ ስነስርዓት ወቅት እንደተናገሩት ሰላም፣ ፍቅር እና ይቅር መባባል ለሁሉም ጥሩ ነው ፡፡ " ሰላም በእጃችን ሳለች አትታወቅም ከእጃችን ከወጣች በኋላ እንጂ፤  ቤተእምነቶች የሰላም ቤትና ምንጭ ናት፤ በመሆኑም  የመለያየትና የመከፋፈል ምክንያትም አይደሉም" ብለዋል። በኃይማኖት ሽፋን ለዘመናት አብሮ ተዋዶና በአንድነት የኖረውን ህዝብ ለመለያያት የሚጥሩ አካላት ስርዓት በማሲያዝ  የህዝቡን ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ ያለፈውን ሁሉ በመርሳት ወደ ቀድሞ ጠንካራ አንድነትና ፍቅር  መመለስ እንደሚገባና ለዚህም እግዚአብሔር ይርዳን በማለት መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡ ከኦሮሚያ እስልምና ምክር ቤት የመጡት ሼህ ሙስባህ ሼህ መሐመድ በበኩላቸው የእስልምና ኃይማኖት አስተምህሮት ሰላም ፍቅርና አንድነት በህዝቦች መካከል እንዲሰፍን መስራት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ህዝበ ሙስልሙ ከክርስቲያን ወንድሞቹ ጋር በመሆን ለሰላም፣ለፍቅርና ለአንድነት እንዲሰሩ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። በህዝቦች መካከል አለመተማመን እንዲኖር ሌት ቀን የሚጥሩ አካላትን ሴራ በማጋለጥ ለህግ ማቅረብ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡ ከጎባ ከተማ ነዋሪዎች መካከል የእርቀ ሰላሙ ተሳታፊ አቶ አለሙ ተፈራ የአካባቢው ህዝብ በኃይማኖት ልዩነት ምክንያት ለችግር ተጋልጧል  ተብሎ የሚናፈሰው ወሬ የተሳሳተና ከእውነት የራቀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ህዝቡ የሁለቱንም ቤተ እምነታቸውን ጭምር ሳይቀር ተጋግዞ በመገንባት በፍቅርና በመተሳሳብ ለዘመናት አብሮ መኖሩ የኃይማኖት ክፍፍል በመካከላቸው እንደሌለ ትልቅ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ሌላው የእርቀ ሰላሙ ተሳታፊና የከተማዋ ነዋሪ ሼክ ካሚል አልይ በበኩላቸው ለዘመናት አብሮ የኖረውን ህዝብ ለመከፋፈል የሚንቀሳቀሱ አካላት በተጀመረው ለውጥ ጥቅማቸው የተነካባቸው መሆኑን ህብረተሰቡ ተገንዝቦ አምርሮ ሊታገላቸው እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡ ችግሩ  ዳግም እንዳይከሰት ስለ ሰላምና አንድነት በመስበክ የድርሻቸውን እንደሚወጡም ተናግረዋል፡፡ በምክትል ፕሬዝዳንት ማዕረግ የኦህዴድ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ አዳነች ሀቤቤ የባሌ ህዝብ ለቀረበው የእርቀ ሰላም ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽና ቀና ትብብርም ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ህብረተሰቡ በኃይማኖትና በብሔር ራሱን ከመከፈፋል በመቆጠብ አንድነቱን በማጠናከር የመከኑ ቡድኖችን አጀንዳን አምርሮ ሊታገላቸው እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ መንግስት በህዝቦች መካከል አለመተማመን እንዲፈጠር በማድረግ ለሰው ህይወትና ንብረት መጥፋት ምክንያት የሆኑ አካላትን ሴራ በማጣራት ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስድም አስታውቀዋል፡፡ የኃይማኖት አባቶች፤ የሀገር ሽማግሌዎችና ቄሮዎች የአካባቢያቸውን ሰላም በመጠበቅ  ለውጡን በላቀ ውጤት ለማጀብና ፍሬ እንዲያፈራ በተደመረ አንድነትና በፍቅር በመስራት ከመንግስት ጎን እንዲቆሙም ጠይቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም