የትህነግ የሴራ ፖለቲካ ስትራቴጂ በጀርመናዊው ምሁር አንደበት

165

የኢትዮጵያን ታሪክና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎችን በቅርበት የሚያውቁ እና በርካታ መጻህፍትን በማዘጋጀት የሚታወቁት ጀርመናዊው አንትሮፖሎጂስት ሊቅ ፕሮፌሰር ኢቮ ሰትሬከር በኢትዮጵያ የሥነ ሰብ ምርምር ዘርፍም በደቡባዊ ኢትዮጵያ ከሚገኙ ብሔር ብሔረሰቦች መካከል የሐመር ሕዝቦች ላይ ትኩረቱን ያደረገ ‹‹The Hamar of Southern Ethiopia›› በሚል ርዕስ ባሳተሙት መጽሐፍ ይታወቃሉ፡፡

ፕሮፌሰር ኢቮ ስትሬከር የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ጉዳዮች በቅርበት የሚከታተሉ ሲሆን እ.ኤ.አ በ1989 በዶክተር መኮንን ቢሻው ጋባዥነት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአንትሮፖሎጂ ትምህርት በሁለተኛ ዲግሪ መሰጠት እንዲቻል ድጋፍ እንዲደርጉ ጥሪ ተደርጎላቸው ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በዘርፉ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን የትምህርት ክፍል አስጀምረዋል።  

ፕሮፌሰር ኢቮ ስትሬከር ከሰሞኑ አንድ ሰፋ ያለ ጽሑፍ ለንባብ አብቅተዋል። የጽሑፉ ርእስ “TPLF Strategies of deceit, a reminder” የሚል ሲሆን ህወሓት በስልጣን ላይ በቆየባቸው ዓመታት ያካሂዳቸው የነበሩ የሴራ ፖለቲካ እንቅስቃሴ በመዳሰስ ትክክለኛ ማንነቱን የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማስገንዘብ ጥረት አድርገዋል።

ከደርግ ውድቀት በኋላ እኤአ በ1991 የመጀመሪያ ዙር የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪዎቻቸውን በመያዝ ወደ ደቡባዊ የኢትዮጵያ አቅጣጫዎችን የከምባታንና የሀዲያ ከፍተኛ ስፍራዎችን በማቆራረጥ በመጓዝ ላይ እያሉ ከተማሪዎቻቸው ጋር ከቀድሞ በተለየ መልኩ ልባቸውን በሚነካ ጉዳይ ላይ በግልጽ ማውራት መጀመራቸውንም ይናገራሉ።

ወደ ኢትዮጵያ ያደረጉት ጉዞ እንዲሁም ያገኟቸው ኢትዮጵያውያን ምሁራን በወቅቱ የደርግ ወታደራዊ መንግስት በህወሃት ተሸንፎ ስልጣኑን ያስረከበበት ወቅት ስለነበር ቀደም ሲል ስለ ህወሃት የነበራቸውን ዕውቀት ይበልጥ የሚያዳብርላቸውን ግንዛቤ ማግኘታቸውን በጽሑፋቸው አመልክተዋል። ከዚህ ባሻገር ትህነግን የሚመለከቱ መረጃዎች ማግኘታቸውንም አያይዘው ገልጸዋል።

ፕሮፌሰር ኢቮ በቅርቡ የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ክልል ተሸሽጎ በርካታ አፍራሽ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርግ በነበረው የሕወሓት ቡድን ላይ የወሰደውን ህግ የማስከበር እርምጃ እና የቡድኑ የቆየ የሴራ ፖለቲካ አራማጅነት አስመልከተው ሰፋ አድረገው በጽሑፋቸው አመልክተዋል።

እርሳቸው በወቅቱ አብረዋቸው ይሰሩ ከነበሩ ኢትዮጵያውያን ምሁራን መካከል ማለትም ከዶ/ር መኮንን ቢሻው፣ ከዶ/ር ፍቃዱ ግዳሙ እንዲሁም የቀድሞ የኢፌዴሪ ፕሬዚደንት  ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ አገኘሁት ባሉት መረጃ መሰረት ህወሃት ሀገሪቱን ሲመራ በነበረበት ወቅትም ሆነ ከዚያ በኋላ ሀገሪቱን ለማተራመስ የሄደበትን ርቀት ዘርዝረዋል።

ትህነግ ያዳበረውን የአመራር ልምድ ተጠቅሞ ለትግራይ ሕዝብ የጦርነት ከበሮ ከመደለቅ ይልቅ ከቀሪው ወገኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ እንዲጠናከር መሥራት ነበረበት ያሉት ፕሮፌሰር ኢቮ፤ ነገር ግን ትህነግ ትኩረት አድርጎ ሲሰራ የነበረው የደርግ ወታደራዊ አገዛዝ ለመጣል በተደረገው ጦርነት ወቅት ተፈጥረው የነበሩ ህዝባዊም ሆነ ፖለቲካዊ አደረጃጀቶችን በማፍረስ እንዲሁም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ኢትዮጵያን በተመለከተ ያለውን መረጃ በተሳሳተ መንገድ እንዲረዳ ሲሰራ ነበር ብለዋል፡፡ 

ፕሮፌሰሩ በጽሁፋቸው ትህነግ ከደርግ ውድቀት በኋላ የሀገሪቱን ሥልጣን በበላይነት በመቆጣጠር የመስፋፋት እና የሀብት ምዝበራው ላይ ከፍተኛ ስራዎችን ሲሰራ ነበር ብለዋል፡፡ በዚህም ትህነግ ወደ ትጥቅ ትግል ከመግባቱ በፊት፣ በትግል ወቅት እንዲሁም ስልጣን ከተቆጣጠረ በኋላ ዲሞክራሲያዊ አስተዳደር ማስፈንን ጨምሮ የተለያዩ ለውጦችን እንደሚያመጣ ለሕዝቡ በርካታ የተስፋ ቃላትን ቢገባም በቃሉ መሰረት አልተገኘም ሲሉ ይገልጻሉ። ትህነግ ከደርግ ስልጣን ከተረከበ በኋላ በሀገሪቱ ዴሞክራሲያዊ እንቅስቃሴ ዙሪያ መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት ሲገባው በተቃራኒው የሽግግር አስተዳደሩን በመመስረት ሂደት ጭምር በሴራ እንዲተበተብ በማድረግ አምባገነንነቱን በጉልህ ማሳየትን መርጧል ብለዋል፡፡

ህወሃት ከሚታወቅባቸው አፋኝ አሰራሮቹ መካከል ዲሞክራሲያዊ አስተዳደር እንዲመሰረት የሚሞግቱ ምሁራንን በማስወገድና በማሳደድ በሀገሪቱ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ እጁን በረጅሙ በማስገባት ጭምር በአሰራራቸው ውስጥ ጣልቃ በመግባት ውጥኑን ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩን ፕሮፌሰሩ አንስተዋል፡፡ በምሳሌነትም እንደነ ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስን የመሳሰሉ የሀገሪቱ አንጋፋ ልሂቃንን በማስወገድ ፍላጎቱን ሲተገብር እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡

ትህነግ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን በመጠቀም ዓላማውን ለማስፈጸም ካለው ፍላጎት የተነሳ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የአገዛዙ ከፍተኛ ባለስልጣናት በቀጥታ እጃቸውን በማስገባት ሲንቀሳቀሱ መቆየታቸውንም በጽሁፋቸው ላይ አመላክተዋል፡፡ የባለስልጣናቱ ሚና ይህ ብቻም እንዳልነበር የሚያነሱት ምሁሩ ለአገዛዙ አንታዘዝም የሚሉ ምሁራንን ሲያባርሩ፣ ሲያሳድዱ እልፍ ሲልም ለእስርና ለስደት ሲዳርጉ ነበር ሲሉ ያብራራሉ። ይህ አይነቱ የምሁራን እንግልት በአማራጭ የፖለቲካ ፓርቲ አባልነትና አመራርነት የሚሳተፉ ምሁራንም ላይ ደርሶባቸዋል ብለዋል፡፡

የደርግ መንግስት ከመውደቁ ከጥቂት ወራት ቀደም ብሎ በኢትዮጵያ ጥናት ማዕከል አስተባባሪነት እና በፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም የመወያያ ጽሁፍ አቅራቢነት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስድስት ኪሎ ግቢ አንድ ዓለም አቀፍ የውይይት መድረክ ተዘጋጅቶ እንደነበር፣ በውይይት መድረኩ ላይም በርካታ ሰዎች ታድመው እንደነበር የጥናት ወረቀቱ ግብም የሰላምና የዕርቅ ኮሚቴ መመስረት እንደነበር ምሁሩ አብራርተዋል፡፡

ትህነግ ደርግን አሸንፎ ከተማ ከገባ በኋላ የሽግግር መንግስት ቻርተር በማዘጋጀት ለውይይት ቢጋብዝም በውይይት መድረኩ ላይ ምሁራን መወከል የሚችሉት በአንድ ቀጥተኛ ተሳታፊ እና በአንድ ታዛቢ ብቻ እንደሆነ በመግለጹ ምክንያት ከምሁራን እና ቀደም ሲል ከተመሰረተው የሰላምና የእርቅ ኮሚቴ መካከል በርካታ ምሁራን እንዳይሳተፉ ክልከላ መጣሉን ገልጸዋል። ኮሚቴው በዚህ ቅሬታ የተሰማው ቢሆንም መድረኩን ካዘጋጁት አካላት የሚለወጥ ነገር ባለመኖሩ ምሁራኑ ሁለት ሰዎችን መርጠው መላካቸውን ዶክተር መኮንንን እማኝ በማድረግ ትህነግ ቀደም ሲልም የሴራ ፖለቲካ አራማጅ እንደነበር በመጥቀስ ጽሁፋቸውን ያጠናክራሉ፡፡

እንደ ፕሮፌሰሩ ጽሁፍ ከሆነ ትህነግ እና መሰል የነጻ አውጭ ቡድኖች የደርግን ከስልጣን መወገድ ተከትሎ የሽግግሩ መንግስት ቻርተር ቢያዘጋጁም ምሁራኑ በውይይት ወቅት በጥልቀት እንነጋገርበታለን ብለው ተስፋ ቢያደርጉም ይህ እንዳልተደረገ ያብራራሉ። በቻርተሩ ዙሪያ በቂ ውይይት ለማድረግ አስቀድሞ የመወያያ አጀንዳ ሊሰጥ ይገባ እንደነበር ያመለከቱት ፕሮፌሰር ኢቮ ይህ ካለመደረጉም በላይ በውይይት ወቅትም ከመድረኩ ይቀርብ የነበረው በእያንዳንዱ አንቀጽ ሳይሆን በጥቅል ያውም በወፍ በረር መልክ እንደነበር ገልጸዋል። ሁሉም ነገር በአዳራሽ ውስጥ እንዲያልቅ መደረጉ በተለይ ራስን በራስ ማስተዳደር እስከመገንጠል በሚለው አንቀጽ ላይ በዝርዝር እንዲወያዩ በቂ ጊዜ አለመሰጠቱን ዶክተር መኮንን ቢሻው እንደነገሯቸው በጽሁፋቸው አስፍረዋል፡፡ 

የትህነግ የሻጥር አካሄድ በሽግግር መንግስት ማቋቋሚያ ቻርተር ውይይት ወቅትም በጉልህ የተንጸባረቀ እንደነበር ፕሮፌሰሩ ያመላከቱ ሲሆን ለማሳያነትም ከዋናው የውይይት መድረክ ቀደም ብሎ በዋና ዋና አጀንዳዎች ላይ የራሱ ቡድኖችን በማወያየት በዋናው የውይይት መድረክ ላይ ጥልቅ ውይይት ሳይካሄድ የድጋፍ አስተያየትና ድምጽ እንዲሰጡ በማድረግ ተጽዕኖ እንዲያሳድሩ የወቅቱ የሽግግር መንግስቱ ፕሬዚደንት ያደርጉ እንደነበር በዚህም የሽግግር መንግስቱ ማቋቋሚያ ቻርተር ጥልቅ ውይይትና ማሻሻያዎች ሳይደረጉበት እንዳለ እንዲጸድቅ መደረጉን ምንጫቸውን ጠቅሰው በጽሁፋቸው አመላክተዋል፡፡

በወቅቱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን በመወከል በውይይቱ ላይ ሲሳተፉ የነበሩት ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ራስን በራስ የማስተዳደር እስከመገንጠል የሚለውን አንቀጽ በብርቱ ሲተቹ የነበሩ በመሆኑ ፖለቲካዊ ጥቃት ኢላማ ውስጥ እንዲገቡ ተደርገዋል ሲሉ በጽሁፋቸው ገልጸዋል፡፡

የወቅቱ የሽግግር መንግስት ፕሬዚደንት የነበሩት መለስ ዜናዊ ሰነዱ ላይ ህዝቡ እንዲወያይ እንደሚደረግና ግብዓት እንደሚታከልበት በተደጋጋሚ መግለጻቸው የሚገልጹት ፕሮፌሰሩ፤ ነግር ግን የውይይት መድረኩ እንደተጠናቀቀ ህዝብ ሳይወያይበት ጊዜያዊ መንግስት የነበረው አካል በአንድ ለሊት ራሱን ለሁለት ዓመታት የሚቆይ የሽግግር መንግስት ቀይሮ ብቅ ማለቱን፣ የራሱን ካቢኔ በማቋቋምም ወደ ስራ መግባቱን በአጠቃላይ ቀደም ሲል የገባውን ቃል ማጠፉን ተንተነው ጽፈዋል፡፡ 

ትህነግ ስልጣኑን እንዲህ ባለ አሻጥር ከተቆናጠጠ ከጥቂት ቀናት በኋላ ምንም እንኳን ለሁለት ዓመታትም ቢሆን የህዝብ ውክልና የሌላቸውን ሚኒስትሮች መሾም በመጀመሩና በቻርተሩ ላይ ህዝብ ሳይወያይበት የተካሄደ የስልጣን ለውጥ በመሆኑ ምክንያት የተወሰኑ ምሁራን በጉዳዩ ላይ ያላቸውን ቅሬታና ትችት ማቅረብ መጀመራቸውን ዋቢ በመጥቀስ አብራርተዋል። 

ምሁሩ ህወሃት ከጥንትም ጀምሮ ለሠላም ያለው አተያይና የሚሰጠው ግምት በጣም ትክክል ያልነበረ መሆኑን የጠቀሱ ሲሆን አሁንም ካለፈ ተሞክሮው ባለመማሩ በዚህ ወቅት በውድቀቱ ዋዜማ ላይ ሆኖ እንኳን ከሰላም ይልቅ ለጦርነት ቅድሚያ በመስጠት ለህዝቡ የጦርነት ነጋሪት ሲጎስም መታየቱን ገልጸዋል። የትግራይ ክልል ህዝብ ወደ ጦርነት እንዲገባ ሲያነሳሳ እንደነበር የገለጹት ፕሮፌሰር ኢቫ ይህም ቀደም ሲል ጀምሮ ሲዘጋጅበት የነበረ ስለመሆኑ አብራርተዋል።

በህወሃት ትህነግ የተሳሳተ የጦርነት ስሌት እና ለህዝቡ እያቀረበ የነበረው የጦርነት ጥሪ በትግራይ ህዝቦችና በተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ መካከል የነበረውን ጠንካራ የሕዝብ ለህዝብ ግንኙነት ሊጎዳው እንደሚችል ጠቅሰው ይህንን የቀደመ ጠንካራ የእርስ በእርስ ግንኙነት ሊያሻክሩ የሚችሉ የተሳሳቱ መንገዶችን በማረም ከሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች ጋር የነበረውን የቀደመ ጠንካራ የግንኙነት ትስስር ማስቀጠል የሚችሉ ስራዎች መስራት ይገባል ሲሉ ምሁሩ ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡

ምንጭ፡- ዎርልድ ፒስ ፋውንዴሽን

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም