በማረሚያ ቤቶች የደረሰው ቃጠሎ የምህረት አዋጁ በማይመለከታቸው ፍርደኞች አቀነባባሪነት የተፈፀመ ነው... አቶ ንጉሱ ጥላሁን

65
ባህርዳር ሀምሌ 19/2010 በአማራ ክልል ሦስት ማረሚያ ቤቶች የተከሰተው የሳት ቃጠሎ ሰሞኑን በፌዴራል መንግስት የጸደቀውን የምህረት አዋጁ ሰበብ በማድረግ አዋጁ በማይመለከታቸው ታራሚዎች አቀነባባሪነት የተፈፀመ መሆኑን የአማራ ክልላዊ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አስታወቀ። የጽፈት ቤቱ ዳይሬክተር አቶ ንጉሱ ጥላሁን ትላንት በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት በፍኖተ ሰላም፣ ወልድያና ደብረ ማርቆስ ማረሚያ ቤቶች የደረሰው ቃጠሎ  የምህረት አዋጁ በማይመለከታቸው ፍርደኞች የተፈፀመ መሆኑ ተደርሶበታል ። በማረሚያ ቤቶቹ  የደረሰው ቃጠሎ  በታራሚዎች ላይ የአካል ጉዳት እንዳደረሰና ከባድ የንብረት ውድመት እንደተከሰተ ጠቁመዋል ። የምህረት አዋጁ የማይመለከታቸው የህግ ታራሚዎች የሚፈጥሩት ህገ- ወጥ ድርጊት የታራሚዎችን መጠለያና መጠቀሚያ ቁሳቁስ ከማውደም በተጨማሪ በቅርቡ በይቅርታ ሊፈቱ የሚችሉ ታራሚዎችን ሊያዘገይ የሚያስችል ሁኔታ መፍጠሩን ተናግረዋል። ችግሩ ወደ ሌሎች ማረሚያ ቤቶች እንዳይዛመት የክልሉ ጸጥታ ኃይል በቂ ዝግጅት ማድረጉን የጠቆሙት አቶ ንጉሱ ይህ ከመሆኑ በፊት ሌሎች ታራሚዎች በህገ- ወጥነት ከተሰማሩ ታራሚዎች ጋር መተባበር እንደሌለባቸው አስገንዝበዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ መሪነት የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴን ለመደገፍ በክልሉ የተካሄዱት ሰልፎች በተሳካ ሁኔታ የተጠናቀቁ በመሆናቸው ሁለተኛና ሦስተኛ ሰልፍ ማካሄድ የማይቻል መሆኑን አቶ ንጉሱ አስታውቀዋል ። ሰልፍ እናካሂዳለን ተብሎ የሚቀርበው ጥያቄ ተገቢነት የሌለው መሆኑንም ገልጸዋል። አቶ ንጉሱ ዛሬ በሰጡት መግለጫ  እንዳሉት " በሁሉም የክልሉ ወረዳዎች ከአንድ ወር በላይ በሆነ ጊዜ ውስጥ የጠቅላይ ሚኒስትሩን የለውጥ እርምጃ ለመደገፍ ህዝቡ ባቀረበው ጥያቄ መሰረት ፈቃድ ተሰጥቶ ሰልፎቹ በስኬት ተጠናቀዋል " ሰልፍ በተካሄደባቸው አንዳንድ አካባቢዎች ድጋሚ ሰልፍ እናካሂድ በሚል ለሁለተኛና ለሦስተኛ ጊዜ እየቀረበ ያለ ጥያቄ አግባብነትና ተቀባይነት የሌለው መሆኑንም ተናግረዋል። ማንኛውም የክልሉ ነዋሪ ለውጡን ለማስቀጠል የሚችለው በተደጋጋሚ ሰለፍ በመውጣት ሳይሆን በልማት ሥራዎች ላይ ጊዜውን፣ ጉልበቱንና እውቀቱን በማበርከት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጎን መሰለፉን በተግባር ሲያረጋግጥ ብቻ መሆኑን ገልፀዋል ። የክልሉ መንግስት ከዚህ በኋላ ለሚቀርብ መሰል የድጋፍ ሰልፍ ጥያቄ ፍቃድ የማይሰጥ መሆኑንም አቶ ንጉሱ አስታውቀዋል ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም