"አድዋ ኢትዮጵያውያንን ያስተሳሰረ የገድል ታሪክ"

1198

ሰውነት ጀምበሩ (ኢዜአ)

በበርካታ ድልና የአርበኝነት ታሪኮች በዓለም መድረክ በሰፊው ትታወቃለች። በዚህም ነፃነቷንና ክብሯን በማስጠበቅ ለአፍሪካ ብሎም ለዓለም ቀንዲል ነች፤ኢትዮጵያ። ዓለም በቅኝ ገዢዎች ፉክክር በከፍተኛ ቀውስ ውስጥ በገባችበት በ19ኛው ክ/ዘመን ኢትዮጵያ ነፃነቷን አስከብራ የኖረች ብቸኛ የአፍሪካ አገር መሆኗ በጉልህ ይነሳል። የውጭ ወራሪ ኃይል አገሪቷን ለመድፈር በመጣ ቁጥር ሁሉም ዜጋ ከዳር እስከዳር በመነቃነቅ በአንድነትና በአብሮነት በመሰለፍ ጠላትን አሳፍሮ መልሷል።

የታሪክ ምሁራን አድዋን ሲገልጹት “የኢትዮጵያውያን አንድነት መገለጫ፣ የመላው ጥቁር ሕዝቦችና የነፃነት ታጋዮች የድል ታሪክ ነው” ይሉታል። የአድዋ ድል ከኢትዮጵያ አልፎ መላው አፍሪካውያን ለነፃነታቸው እንዲተጉና አንድነታቸውን እንዲያጠናከሩ መሰረት የሆነ ታላቅ ድል ስለመሆኑም ይናገራሉ። የጥቁር ህዝቦች የአሸናፊነት ማሳያም ተደርጎም ይወሰዳል-የአድዋ ድል።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት በደቡብ አፍሪካ ናሽናል ሪሰርች ፋውንዴሽን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ስራ ክፍል ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ማሞ ሙጬ የአድዋ ድል ለመላው አፍሪካውያን የህብረትና የአንድነት ተምሳሌት መሆኑን ይናገራሉ። ከዚህ ባሻገር የአድዋ ድል የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ መሰረት ከሆኑ ምክንያቶች አንዱና ዋነኛው ስለመሆኑም አክለው ይገልጻሉ። የአፍሪካ ህብረት ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ እንዲሆን ምክንያት ከሆኑ ጉዳዮች መካከልም አድዋ በቀዳሚነት ይጠቀሳል።

በዩኒቨርሲቲ ኦፍ በርሊን መምህር የሆኑት ዶ/ር ፍቃዱ በቀለ “አድዋ ለእኛ የሚሰጠን ትርጉም ምንድነው? እኛስ ከአድዋ ምን ተማርን?” በሚል ርእስ በፃፉት ትንታኔ ላይ የአድዋን ድል ከፍተኛ የሚያደርገው አባቶቻችን እጅግ ወደ ኋላ በቀረ መሳሪያ በመታገዝ የተሻለ የአደረጃጀት ስልት የነበረውን ወራሪ የጣሊያን ኃይል ቅስሙን ሰብረው ማባረራቸው ነው በማለት ያብራራሉ። ጣሊያን በአድዋ ላይ ከተሸነፈ በኋላ አርባ ዓመት ያህል ዝግጅት አድርጎ እንደገና ኢትዮጵያን ለመውረር ቢመጣም ኢትዮጵያውያን በጋራ በመቆም ለጠላት አንድም ፋታ ሳይሰጡ ድል መንሳታቸውን ይገልጻሉ።

ዘንድሮ 125ኛው የዓድዋ ድል በዓል “አድዋ የሕብረ ብሔራዊ አንድነት ዓርማ” በሚል መሪ ሃሳብ ይከበራል። ከበዓሉ አከባበር ጋር በተያያዘ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ያዘጋጀው "ቱባ ወግ" በተሰኘ መድረክ ላይ ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረቡት የታሪክ ምሁሩ ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው እንደገለጹት ጣሊያን ኢትዮጵያውያንን ለመከፋፈል ትልቅ ሚና ስትጫወት ነበር። ለዚህም በአጼ ሚኒሊክ ዘንድ ቁርሾ ያላቸውን መሳፍንት ወደ እነሱ በማዞር የመከፋፈል ፖሊሲን ዘርግተው ይሰሩበት እንደነበር ተናግረዋል።

ይህ ሁኔታ ለጊዜው የሰራ ቢመስልም በሂደት ግን ኢትዮያዊያን በአገራዊ አንድነት ላይ የማይደራደሩ መሆናቸውን አሳይተዋል ብለዋል። አንድነት ሲባል ጭንቅ በሆነ ወቅት በተለያዩ መንገዶች አገርን ማስቀደም፤ ለአገር ታማኝ ሆኖ መኖር ማለት ነው በማለትም አብራርተዋል። በዚሁ መድረክ ላይ ሌላኛው ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረቡት የታሪክ ምሁር ዶክተር አህመድ ሀሰን የአድዋ ተጋድሎ መቻቻልን በአብሮነት ያሳየ መገለጫ መሆኑን ገልጸዋል። የአድዋ ድል ዓላማውም ሆነ ተጋድሎው የጋራ መሆኑን በተምሳሌነት የተረጋገጠ ድል ነው ብለውታል።

የአድዋ ድል ሁሉም ኢትዮጵያዊ ደምና አጥንቱን የገበረበት ነው። ህዝቡ በህብር ተሰልፎ ከጫፍ እስከ ጫፍ የተመመበትና ጠላትን ያሳፈረበት ድል ነው። የአድዋ ድል ለአሁኑ ትውልድ አብሮነትን፣ ህብረትን፣ መደማመጥንና በጋራ መቆምን ያስተምራል። ኢትዮጵያውያን በብሔር፣ በሃይማኖት፣ በባህልና በቋንቋ ወዘተ ሊለያዩ ይችላሉ፤ ነገር ግን በጋራ አጀንዳዎች ዙሪያ ዘመናት የተሻገረና ሌላው ዓለም ትምህርት የወሰደበት የአብሮነት እሴት አላቸው። ይህንን መልካም እሴት ሊንከባከቡትና ጠብቀው ሊያቆዩት ይገባል።

ሀገራችን አሁን ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ ስንመለከት በአንድ በኩል በውስጥና በውጭ ኃይሎች ሴራ አገርን የማተራመስና ብሎም የማፍረስ ጥረት ከመቼውም ጊዜ በላይ የታየበት፤ በሌላ በኩል ደግሞ ከድህነትና ኋላ ቀርነት ጋር ከፍተኛ ግብግብ ውስጥ የተገባበት ነው። በዚህ ወቅት አገርን መታደግ የሚቻለው በአንድነት በመቆም ብቻ ነው። ሀገሪቷን ከወቅታዊ ፈተናዎች መታደግ እና የበለጸገችና ለዜጎቿ ምቹ የሆነች አገር ለቀጣዩ ትውልድ ማስረከብ ከአድዋ ድል የምንማረው ሌላኛው ገጽታ ነው።

አሁን የተጋረጡብን ችግሮች ልንፈታ የምንችለው ስንደማመጥና አንድ ሆነን ስንቆም ብቻ ነው። አለበለዚያ የሚገጥሙን ማናቸውም ፈተናዎች የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ሊያንበረክኩን እንደሚችሉ ግልጽ ነው። “ካልተደራጀ ትልቅ ሀገር የተደራጀች ትንሽ መንደር ትልቅ ስራ ትሰራለች” እንደሚባለው ችግሮቻችንን ለመወጣት በአንድነት አብሮ መቆም ምን ያህል ትርጉም እንዳለው የአድዋ ድል ህያው ማሳያ ነው።

ኢትዮጵያ ዜጎቿ በአንድነት የሰሯት፣ አንድነታቸውን ያስመሰከሩባት፣ በጥረታቸው ነፃነቷን ጠብቀው ለትውልዱ ያቆዩዋት አገር ነች። አድዋ የአባቶችን ታሪክ ተገንዝቦ፤ ያወረሱንን መልካም ገጸ በረከት ማስቀጠልና ለቀጣዩ ማስተላለፍ የሚችል ትውልድ መሆን እንደሚገባን ያስታውሰናል። የአድዋ ድል ስኬታማ የሆነው በመላ ኢትዮጵያውያን የአንድነት መንፈስ በመሆኑ አሁንም ሆነ ወደፊት የአገራችንን እድገትና ብልጽግና የምናረጋግጠው አንድ ላይ በመቆም ብቻ ነው። ሰላም!

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም