የአድዋ ድል የኢትዮጵያውያን አንድነት ማሳያ መሆኑን የሚዛን አማን ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ

67

ሚዛን፣ የካቲት 11/2013( ኢዜአ)  የአድዋ ድል ኢትዮጵያዊያንን በጋራ ያሰለፈ የአንድነት ምሳሌ ማሳያ መሆኑን በቤንች ሸኮ ዞን ሚዛን አማን ከተማ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች ተናገሩ።

ነዋሪዎቹ እንዳሉት አሁን ያለው ትውልድ  ሉዐላዊነትን ለማስጠበቅ በአድዋ ከተከፈለው መሰዋትነት ሀገሩን ለመገንባትና ለሠላም ሊጠቀምበት ይገባል።

የከተማዋ ነዋሪ አቶ ዘለዓለም ልክያለው በሰጡት አስተያየት "አድዋ ቀለም ፣ጎሳና ሃይማኖት የሌለውና ምንም የተመቻቸ ነገር ሳይኖር የሀገር ክብርና ፍቅር ብቻ በመያዝ ድል ማድረግ የተቻለበት  አኩሪ ገድል ነው " ብለዋል።

የአድዋ ድል  ኢትዮጵያዊያን አሁንም  የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን  ማለፍ እንደሚቻሉ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።

አቶ ታጠቅ ከበደ በበኩላቸው የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ምሳሌ የሆነው የአድዋ ድል ምንጊዜም ትውልድ ሊዘክረው የሚገባው ገድል መሆኑን ገልጸዋል።

"በአድዋ እኔ ብቻ የሚል ወይም ግለሰባዊ ሀሳብ ሳይሆን ሀገራዊ ማንነት ብቻ ተይዞ አኩሪ ውጤት ተመዝግቧል" ብለዋል።

የአድዋ ድል  የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን የመላው ዓለም ጥቁር ህዝቦች ቀና ብለው እንዲሄዱ ያስቻለ መሆኑን የተናገረችው ደግሞ የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ ተማሪ ሜሎዲ ተመስገን ናት።

"ዛሬም ትኩረታችንን አንድነታችን ላይ በማድረግ ኢትዮጵያዊ ማንነታችንን ማስቀጠል አለብን" ብላለች።

ለዚህም ከንግግር ያለፈ ተግባር እንደሚያስፈልግ ገልጻለች።

የህግ ባለሙያው አቶ በረከት ደሳለኝ በበኩላቸው፤ "ድሉን ስንጎናጸፍ ብዙ ስልጠናና ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ውጤት ኖሮን አይደለም፤  ኃይልና ጉልበት የሆነን የኢትዮጵያዊ የአንድነት ስሜታችን ነው" ብለዋል።

ዛሬ  ከዛ የተሻለ አቅም  ቢኖርም  በብሔርና ቀለም እየተከፋፈሉ መቀጠል እንደ አድዋ ያለ ሌላ ድል ማስመዝገብ እንደማይቻል ጠቁመዋል።

የትናንት ማንነታችን አብቦ እንዲያፈራ በሁሉም መስክ አንድ ሆኖ መቆምና መተሳሰብን ከአድዋ ተምረን ልንተገብረው ይገባል ብለዋል።

የታሪክ መምህሩ ደነቅ ደሳለኝ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያውያን የተባበረ ክንድ ነጮች ለመጀመሪያ ጊዜ በጥቁሮች መሸነፋቸው  የጥቁር ህዝቦች ጀግንነት የተመሰከረበት ድል መሆኑን ገልጸዋል።

አሁን ያለው ትውልድ ለሀገር ሉዐላዊነት እና የብልጽግና ጉዞ ስኬት አንድ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል።

የድል በዓሉን ዓመት ቆጥሮ ከማክበር ባለፈ ትውልዱ እንዲማርበት በትምህርት ቤቶች መሰራት እንዳለበት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም