ለመጀመሪያ ጊዜ በመስኖ የጀመርነው የስንዴ ልማት ያልጠበቅነውን ተስፋ ሰጥቶናል- አርሶ አደሮች

157

መቱ፣ጅማ የካቲት 10/2013 (ኢዜአ) በመስኖ በመታገዝ ለመጀመሪያ ጊዜ በተሰማሩበት የስንዴ ልማት ያልጠበቁትን ተሰፋ ማግኘታቸውን በጅማና ኢሉአባቦር ዞኖች አርሶ አደሮች ገለጹ።

በዞኖቹ በተያዘው በጋ ወቅት ለመጀመሪያ ጊዜ በመስኖ በመታገዝ 29 ሺህ 500 ሄክታር መሬት ላይ የስንዴ ልማት እየተካሄደ ነው ።

በጅማ ዞን የጌራ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር መኑ አባ ሳምቢ ለኢዜአ እንደገለጹት ከዚህ ቀደም በመኸር ወቅት ከሚያለሙት በቆሎ በስተቀር ሌላ ሰብል አልመተው አያውቁም ።

"በዚህ አመት በጋ ወቅት በመስኖ ስንዴ አልሙ ስንባል ማመን አልቻልንም ነበር፤ ስንገባበት ግን የሚቻል ሆኖ አግኝተነዋል" ብለዋል።

ከዚህ ቀደም ለመኽር እርሻ ይጠቀሙበት በነበረው አራት ሄክታር ማሳ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ በመስኖ በመታገዝ የዘሩት ስንዴ የሰብሉ ይዘት ተስፋ ሰጭ ሆኖ እንዳገኙት ገልጸዋል።

መንግስት ባቀበላቸው ዘርና የሞተር ፖምፕ በመታገዝ በአካባቢያቸው ከሚፈሱ የናሶና ጀርማ ወንዞች ውሀ በመሳብ የመስኖ ልማቱን እያካሄዱ መሆናቸውን ተናግረዋል።

እንደ አርሶ አደር መኑ ገለጻ በመስኖ የጀመሩት የስንዴ ልማት ለወደፊት ተጨማሪ የገቢ ምንጭ እንደሚሆናቸው ተስፋ አድርገዋል።

“ከዚህ በፊት በመኽር ከምናመርተው በቆሎ በስተቀር  ስንዴን ሞክረንም ሆነ አስበነው አናቅም” ያሉት ደግሞ  በዞኑ የማና ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ጊዲ አባቡልጉ ናቸው።

የአካባቢው ነዋሪ ከመኽር ባሻገር በበጋ ወቅት በመስኖ የጓሮ አትክልትና ፍራፍሬ የማምማት የጎለበተ ልምድ እንዳለው የገለጹት አርሶ አደር ጊዲ በዚህ አመት ልምዳቸውን በመጠቀም ለመጀመሪያ ጊዜ ስንዴን በመስኖ ማልማት መጀመራቸውን ተናግረዋል ።

"አሁን ላይ በመስኖ የዘራንውን ስንዴ በማሳ ላይ ስናየው ተስፋ ሰጥቶናል፤ ለወደፊትም ልማቱን በማጠናከር ለገቢ ምንጭነት እንደምንጠቀምበት እምነት አለኝ" ሲሉ አርሶ አደሩ ተስፋቸውን ገልጸዋል።

የዞኑ የግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ መስፍን ረጋሳ በዞኑ በ20 ወረዳዎቸ በ28 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ስንዴ እየለማ መሆኑን ተናግረዋል።

በዞኑ በበጋው ወቅት 30ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ስንዴን በመስኖ ለማልማት ታቅዶ 94 በመቶ ማከናወን መቻሉን አመልክተዋል፡፡

እንደ ሀላፊው ገለጻ  በልማቱ 53 ሺህ 910  አርሶአደሮች፣ ስራ አጥ ውጣቶችና  ባለሀብቶች በመሳተፍ ላይ ሲሆኑ ከልማቱ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል።

በግብርና ምርምር እንስቲትዩት የስንዴ ተመራማሪ አቶ ሽመልስ አለማየሁ እንዳሉት ስንዴ በባህርይው ብዙ ዝናብ ስለማይፈልግ መስኖን በመጠቀም ሰብሉን ማልማት ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ አተዋጽኦ አለው ።

አብዛኛው የዞኑ የአየር ጠባይ ለስንዴ ሰብል የተመቸ በመሆኑ ልማቱን በማስፋፋት ላይ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ ተመራማሪው አመልክተዋል።

በተመሳሳይ በኢሉባቦር ዞን በተለያዩ ወረዳዎች በግልና በማህበር ተደራጅተው ለመጀመሪያ ጊዜ በመስኖ ስንዴ በማምረት የጀመሩ አርሶ አደሮችም ልማቱ ተስፋ ሰጭ መሆኑን ተናግረዋል ።

መቱ ወረዳ የቦቶ ቀበሌ ነዋሪ  አርሶ አድር ብርሃኑ ተገኝ እንደገለጹት በአካባቢያቸው ስንዴ ይለማል የሚል እምነት እንዳልነበራቸውም።

አሁን ላይ በጀመሩት በመስኖ ስንዴን የማልማት ሥራ ያልጠበቁትን ተስፋ እንደሰጣቸው ተናግረዋል።


ከውጭ የሚገባን ስንዴ በሀገር ውስጥ አቅም ለመተካት ሲታቀድ በአከባቢያቸው ስንዴን ማልማት እንደማይቻል ያስቡ እንደነበር  የገለጹት ደግሞ የቀበሌው ነዋሪ አርሶ አደር  ሙሉጌታ ብርሃኑ ናቸው።

ወደ ስራ ከገቡ በኋላ እያዩት ያለው ውጤት በተለየ ተስፋ ሰጭ ሆኖ እንዳገኙት ተናግረዋል ።

በአካባቢው ስንዴን ማልማት ታስቦም ተሞክሮም እንደማያውቅ የገለጹት  ደገሞ  የወረዳው የግብርና ልማት ባለሙያው አቶ አብዱራሂም መሐመድ  ናቸዉ።

ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጀመረው  በመስኖ ስንዴን የማልማት ስራ ውጤታማነት አርሶ አደሮቹን በሙያቸው እየደገፉ መሆኑን ተናግረዋል።

በዞኑ ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት የእህል ምርትና ችግኝ ጥበቃ የሥራ ሂደት ባለቤት አቶ ተፈሪ ረጋሳ  በበኩላቸው በበጋው ወቅት በመስኖ በመታገዝ  1ሺህ 500 ሄክታር መሬት ላይ ስንዴ ለማልማት ታቅዶ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም