የአድዋ ድል ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሊማርበት የሚገባ ታሪካዊ ክስተት ነው-የአምቦ ወጣቶች

89

አምቦ፣ የካቲት 10/2013-(ኢዜአ) የኢትዮጵያዊያንና የአፍሪካዊያን ኩራት ከሆነው የአድዋ ድል ሁሉም ዜጋ ሊማርበት የሚገባ ታሪካዊ ክስተት ነው ሲሉ የአምቦ ከተማ ወጣቶች ገለጹ።

ጀግኖች አባቶች ልዩነታቸውን አቻችለው ለሀገር ክብርና ነፃነት በአንድነት በመቆም ከተጎናጸፉት የአድዋ ድል ሁሉም ሊማርበት እንደሚገባ ወጣቶቹ ለኢዜአ አስታውቀዋል።


ከወጣቶቹ መካከል ቢሊልኝ መላኩ እንደገለጸው ጀግኖች ኢትዮጵያውያን ከሁሉም የሀገሪቱ ጫፍ በአንድነት በመነሳት ለሃገራቸው ነፃነት፣ ክብርና ሉአላዊነት መከበር በአድዋ ታላቅ ታሪካዊ ድል አስገኝተዋል፡፡

"እኛም ወጣቶች ባንድነት በመተባበር አባቶቻችን ያኖሩልንን ድል በመንከባከብ ሀገራችንን ማስከበር አለብን " ብሏል።

"ኢትዮጵያ የኢጣሊያን የቅኝ ግዛት ሙከራ አልቀበልም ያለች ብቸኛዋ አፍሪካዊት ሀገር ነች " ያለው ደግሞ ወጣት ፈጠነ ባልቻ ነው፡፡

ወጣቱ እንዳለው የኢትዮጵያዊያንና የአፍሪካዊያን ኩራት ከሆነው ከአድዋ ድል ልምድ በመውስድ ሀገራችን በጋራ መጠበቅ ይገባናል፡፡

"የአድዋ ድል የነጭ የበላይነት ስነልቦናን የሰበረና አውሮፓዊያንን እጅ ያሰጠ ነው"  ብሏል።

ዶክተር መንግስቱ ሌንጮ በበኩሉ “የአድዋ ድል መቼም ችላ የማይባል ጎልቶ የሚታይ የነጻነት ተጋድሎና ነጮች በጥቁሮች ላይ የነበራቸውን የበላይነትን የቀየረ ነው” ሲል ገልጾታል።

''ድሉ ኢትዮጵያውያን ሉአላዊነታችንንና  ነጻነታችንን ያስከበርንበት የአንድነታችን መገለጫ መሆኑን ተናግሯል ።

ድሉ ሁሉም ኢትዮጵያውያን አንድ በመሆን በጀግንነት “እምቢ ለሃገሬ” ብለው በፍጹም ሀገር ወዳድነት  መንፈስ ተባብረው የተጎናጸፉት በመሆኑ ሁሉም ሊማርበት እንደሚገባ አመልክቷል።

ጀግኖች ኢትዮጵያዊያን በነፃነት መኖር የሚቻለው ሀገር ታፍራና ተከብራ ስትቆይ መሆኑን በማመን ልዩነታቸውን አቻችለው አድዋ ላይ ከተቀዳጁት ድል ሁሉም ዜጋ ሊማር እንደሚገባ አስታውቋል፡፡

ኢትዮጵያውያን ከአድዋ ጀግኖች መተባበርንና መደማመጥን እንዲሁም የሀገር ፍቅርን በመረዳት ወቅታዊ ችግሮችን በአሸናፊነት የመወጣት ልምድን ልንማርና ልናዳብር ይገባል" ብሏል ዶክተር መንግስቱ ።

እንደ አስተያየት ሰጭዎቹ ገለጻ የአድዋ ድል ልዩነቶችንና ጥላቻን በማስወገድ ሀገራዊ አንድነትና አብሮነትን ለማጠናከር የሚያስተምር ታሪካዊ ክስተት ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም