ደባርቅ ዩኒቨርሲቲ 14 የትምህርት ተቋማትን የዲጂታል ላይብራሪ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ ነው

99

ጎንደር፣ የካቲት 10/2013 (ኢዜአ ) ደባርቅ ዩኒቨርሲቲ 14 የትምህርት ተቋማትን በማህበረሰብ አገልግሎት ፕሮግራም የዲጂታል ላይብረሪ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ገለጸ፡፡

የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዘዳንት ፕሮፌሰር ተሰማ ዘውዱ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በትምህርት ተቋማቱ ቴክኖሎጂውን ተደራሽ ለማድረግ አንድ ሚሊዮን 400 ሺህ ብር ተመድቧል፡፡

የቴክኖሎጂው ተጠቃሚ የሚሆኑት በሰሜን ጎንደር ዞን የሚገኙ 7 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችና 7 የሙያና ቴክኒክ ኮሌጆች መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

በቴክኖሎጂውም በዞኑ የሚገኙ በሰባት ወረዳዎችና ሁለት የከተማ አስተዳደሮች የሚገኙ ከ10ሺ በላይ የተቋማቱ ተማሪዎችም ተጠቃሚ እንደሚሆኑም አስረድተዋል፡፡

በትምህርት ተቋማቱ የሚቋቋሙት ዲጂታል ላይብረሪዎች እያንዳንዳቸው እስከ 90ሺህ የሚደርሱ የመማሪያና የማጣቀሻ መጻህፍት የመያዝ አቅም እንዳላቸውም ገልጸዋል፡፡

የተቋማቱ ተማሪዎች እስከ 1 ኪሎ ሜትር በሚሸፍን ቦታ ላይ በመሆን ታብሌቶችን ፣ላፕቶፖችንና ስማርት ፎኖችን በመጠቀም የመማሪያ መጻህፍትን አውርደው መጠቀም የሚስችላቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በትምህርት ተቋማቱ ለሚያቋቁሟቸው የዲጂታል ላይብራሪዎች 140 ዴስክቶፕ ኮምፒውተሮችን ለማሰራጨት ማቀዱን ፕሮፌሰር ተሰማ አመልክተዋል፡፡

ዲጂታል ላይብራሪዎቹ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ አጋዥ እንደሚሆኑ ጠቁመው ፤ የላይብረሪዎቹ የማቋቋም ስራ በመጪው መጋቢት ወር ላይ በማጠናቀቅ ለአገልግሎት እንደሚበቁም አስረድተዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ለሚያቋቁመው ዲጂታል ላይበራሪ አራት ክፍሎች በደባርቅ ከተማ በሚገኙ ሁለት የመሰናዶና ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መዘጋጀታቸውን የተናገሩት ደግሞ የከተማው ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተመስገን ፈንታ ናቸው፡፡

ዲጂታል ላይብራሪው ተማሪዎችን በትምህርታቸው የተሻለ ውጤት እንዲያመጡ እንደሚያግዝ ጠቁመው፤ ከዩኒቨርሲቲው ጋር በመቀናጀት እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም