ህግ በማስከበር ምርጫው ሠላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ የፍትህና ፀጥታ አካላት ገለጹ

77

ድሬዳዋ፣ የካቲት 9/2013(ኢዜአ) መጪው ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ ህግን በማስከበር ሠላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን የምስራቅ ተጎራባች ክልሎች የፍትህና ፀጥታ አካላት ገለጹ።

የፍትህና ጸጥታ አካላቱ በምስራቅ የሀገሪቱ ክፍል አስተማማኝና ዘላቂ ሰላም ለመፍጠር የሚያከናውኗቸውን ተግባራት ለማጠናከር በድሬዳዋ ግምገማ አካሄደዋል።

ከግምገማው መድረክ ተሳታፊዎች መካከል የአፋር ክልል የፍትህና የፀጥታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ መሐመድ አወል በክልሉ አስተማማኝ ሠላም የማረጋገጡን ተግባራት በማጠናከር መጪው ምርጫ ህግን ተከትሎ በሠላም እንዲፈጸም አስፈላጊው ዝግጅት ተጠናቋል ብለዋል፡፡

የሱማሌ ክልል የፍትህ ፀጥታ ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አቶ አብዱላሂ አህመድ በበኩላቸው በክልሉ ለምርጫው በሠላም እንዲጠናቀቅ ለፀጥታ አካላት አስፈላጊው ስልጠና መሰጠቱን ገልጸው፤ የምርጫ ቁሶች ወደ ሚፈለገው የምርጫ ጣቢያዎች በሠላም እንዲደርሱ አስፈላጊው የፀጥታ ስራ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡

ለምርጫው ሠላማዊነትና ዴሞክራሲያዊነት በምርጫው ህግ ላይ በየደረጃው ለሚገኙ የፀጥታ አካላት ተገቢው ስልጠና መሰጠቱን የገለፁት ደግሞ የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽነር አለሙ መግራ ናቸው፡፡

የሀገሪቱ 90 በመቶ የወጪና ገቢ ንግድ እንቅስቃሴዎች በሚካሄድበት የምስራቁ ክፍል በተናጠልና በጋራ አስተማማኝ ሰላም ለመፍጠር እየተሰሩ የሚገኙ ተግባራት ለምርጫው ሰላማዊነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል ብለዋል፡፡

የሐረሪ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር አታሃም አብዲ በበኩላቸው በክልሉ አልፎ አልፎ የሚስተዋሉ የፀጥታ ችግሮችን በመከላከል ሰላም መስፈኑን ገልጸዋል፡፡

መጪው ምርጫ ዴሞራሲያዊና ተአማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የፀጥታ አካላት አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጋቸውን አስታወቀዋል፡፡

የመድረኩ ተሳታፊዎች  በሚጎራበቱባቸው አካባቢዎች የሚስተዋሉ መጠነኛ ችግሮችን በውይይት በመፍታት በጋራና በተናጠል የጀመሩትን ዘላቂ ሰላም  የማስከበር ስራን እንደሚያስቀጥሉ ተናግረዋል፡፡

ከየካቲት 29 እስከ መጋቢት 2/2013 ዓ.ም የሚሰጠው የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ሰላማዊ ሆኖ በስኬት እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጋቸውንም   ገልጸዋል፡፡

የግምገማ መድረኩን የመሩት በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል መከላከል ዘርፍ ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ጄነራል መላኩ ፋንታ በበኩላቸው" ሀገራችን ከለውጡ በኋላ የተደቀነባትን የሰላም ችግሮች ስልታዊ በሆነ መንገድ እየፈታችና የተሻለ ሰላም በአገሪቱ እየተረጋገጠ ይገኛል" ብለዋል፡፡

በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል አስተማሪና ህግን የማስከበር እርምጃ ተወስዶ አገርን የማረጋጋት ወሳኝ ስራ መሰራቱን አውስተዋል፡፡

በዚህ ህግን በማስከበርም ሆነ በየክልሉ ያሉ የህውሃት ጁንታ ርዝራዦችን በቁጥጥር ስር በማዋልና ለህግ በማቅረብ በኩል ክልሎች ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል ብለዋል፡፡

ይህን የተናጠልና የተቀናጀ ስራ በማጠናከር ቀጣዩ ሀገር አቀፍ ምርጫ ከቅድመ እስከ ድህረ ምርጫ ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የምርጫ ህግን በማስከበር ታላቅ ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡

ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ እንዳይሆን ብጥብጥ እንዲፈጠር የሚፈልጉ ከውስጥም ከውጪም የሚገኙ ኃይሎችን ነቅቶ በመጠበቅ ለምርጫው ስኬታማነተ ተቀናጅቶ መትጋት እንዳለባቸውም ተናግረዋል፡፡

ለአንድ ቀን በተካሄደው የግምገማው መድረክ ከአፋር ፣ ሱማሌ፣ሐረሪ ክልሎች ፣ ከኦሮሚያ ምስራቅ፣ ምዕራብ ሐረርጌና ምስራቅ ሸዋ ዞኖች እንዲሁም  ድሬዳዋ አስተዳደርና ከአማራ ሰሜን ሸዋ ዞን የተወጣጡ የፍትህና ጸጥታ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም